አሜሪካ ለሳኡዲ አረቢያ በሚደረግ የመሳሪያ ሽያጭ ላይ ጥላው የነበረውን እግድ ለማንሳት ወሰነች
የየመን ጦርነት ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ ከሚያደርጓቸው በርካታ የእጅ አዙር ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ ይጠቀሳል
አሜሪካ፣ ሳኡዲ አረቢያ በየመን ጦርነት የነበራት ሚና እንዲቀንስ ጫና ለማድረግ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ለማንሳት ከውሳኔ ላይ ደርሳለች
አሜሪካ ለሳኡዲ አረቢያ በሚደረግ የመሳሪያ ሽያጭ ላይ ጥላው የነበረውን እግድ ለማንሳት ወሰነች።
የፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር አሜሪካ ለሳኡዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ እንዳትሸጥ ጥሎት የነበረው ማዕቀብ ለማንሳት መወሰኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚስቴር በትናንትናው እለት አስታውቋል።
አሜሪካ ማዕቀቡን የጣለችው ሳኡዲ አረቢያ በየመን ጦርነት የነበራት ሚና እንዲቀንስ ጫና ለማድረግ ነበር።
አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን እንደተናገሩት ከመሬት ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳይሎችን ለሳኡዲ የመሸጥ እግድ መነሳቱን ማረጋገጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለስልጣኑ እንደገለጹት አሜሪካ ሁኔታዎችን እየገመገመች እና ከኮንቬንሽናል አርምስ ትራስፈር ፖሊሲ ጋር የማይቃረን መሆኑን እያረጋገጠች ለሳኡዲ የጦር መሳሪያ ታስተላልፋለች።
አስተዳደሩ እግዱን ለማንሳት መወሰኑን ለኮኔግረሱ ማስረዳቱን የኮኔግረሽናል ረዳት ተናግረዋል።
"ሳኡዲዎች የሚመለከታቸውን አድርገዋል፤ስለዚህ በእኛ በከል የሚጠበቅብንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል"ሱሉ አንድ ከፍተኛ የባይደን አስተዳደር ባለስልጣን ገልጸዋል። በአሜሪካ ህግ መሰረት ዋናዋና አለምአቀፍ የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነቶች ከመጽደቃቸው በፊት በኮንግረስ ወይም በተወካዮች ምክርቤት ቀርበው መጽደቅ ይኖርባቸዋል።
የዲሞክራት እና የሪፐብሊካን ተወካዮች ሳኡዲ አረቢያ በየመን እያደረገች ባለው ዘመቻ ንጹሃን መገደለቸውን እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመጥቀስ ባለፉት አመታት ለሳኡዲ በሚደረገው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ነገርግን ይህ ተቃውሞ ሀማስ በእስራኤል ላይ ከባድ የተባለውን ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ብጥብጥ ከተነሳ በኋላ ቀዝቀዝ ሊል ችሏል።
የአስተዳደሩ ባለስልጣን እንደናገሩት ሳኡዲ እና የየመኖቹ ሀውቲዎች በተመድ አማካኝነት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ሳኡዲ አረቢያ በየመን ላይ ስትፈጽም የነበረውን የአየር ጥቃት ያቆመች ሲሆን ሀውቲዎችም ወደ ሳኡዲ ግዛት መተኮሳቸውን አቁመዋል።
የየመን ጦርነት ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ ከሚያደርጓቸው በርካታ የእጅ አዙር ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ ይጠቀሳል።
በሳኡዲ አረቢያ የሚደገፈውን የየመን መንግስት በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ ከሰንዓ ያነሱት ሀውቲዎች ከ2015 ጀምሮ በሳኡዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምር ኃይል ሲዋጉ ቆይተዋል። ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመናውያን እንዲገደሉ እና 80 በመቶ የሚሆነው የየመን ህዝብ በእርዳታ ላይ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ባይደን በፈረንጆቹ 2021 ለሳኡዲ በሚደረግ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ እግድ የጣሉት፣ ሳኡዲ በየመን በምታደርገው ዘመቻ በንጹሀን ላይ ከፍተኛ ግድያ አድርሳለች በሚል ምክንያት ነበር።