አሜሪካና ሳኡዲ የኒዩክሌር ሃይልና የደህንነት ትብብር ስምምነት ለመፈራረም ተቃርበዋል
ሳኡዲ ግን ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ማደስ የሚያስችለው ስምምነት ፍልስጤም ነጻ ሀገር ሆና የምትመሰረትበትን ሂደት በግልጽ ማካተት አለበት ብላለች
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ይህን የሪያድ ቅድመ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲቃወሙት ተደምጠዋል
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በኒዩክሌር ሃይል፣ የደህንነት እና መከላከያ ዘርፎች የሚፈራረሙት ረቂቅ ስምምነት ወደመጠናቀቅ መቃረቡ ተገለጸ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ “በሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል” ብለዋል።
ስምምነቱ ሳኡዲ አረቢያ እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ የሚፈራረሙት ስምምነት አካል መሆኑንም ገልጸዋል።
ሪያድ ከቴል አቪቭ ጋር ግንኙነቷን እንድታድስ ዋሽንግተን ሲቪል የኒዩክሌር ሃይል ጣቢያዎችን ለመገንባት ቃል መግባቷ ይታወሳል።
ይህ እውን ሆኖ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማስተካከል ግን ሳኡዲ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።
ከ35 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የጋዛ ጦርነት እንዲቆምና ፍልስጤም ነጻ ሀገር ሆና የምትመሰረትበት ሂደት በስምምነቱ በግልጽ እንዲሰፍር መጠየቋንም ነው ብሊንከን ያነሱት።
አሜሪካ እና ሳኡዲ ስምምነቱን ለመፈራረም ቢቃረቡም ሪያድ ከቴል አቪቭ ጋር ግንኙነት የማደስ ስምምነት ለመድረስ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች በእስራኤል በኩል አሁን ላይ ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የትኛውንም የፍልስጤም የሀገር ምስረታ የሚያካትት ስምምነት አንፈርምም ማለታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በጋዛ ታጋቾች የሚለቀቁበት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረጓን ያወሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን፥ አሁን እስራኤል የመጨረሻውን ውሳኔዋን የምታሳውቅበት ጊዜ ተቃርቧል ብለዋል።
ኔታንያሁ በአጋራቸው አሜሪካ የተመቻቸውን ከሳኡዲ ጋር ግንኙነት የማደስ ታሪካዊ እድል እንዳይጠቀሙ ቀኝ ዘመም አጣማሪ ፓርቲዎች ጫና እየፈጠሩባቸው ነው ተብሏል።
የጋዛውን ጦርነት ማቆም መንግስታቸውን ማፍረሱና ከስልጣናቸው ማሰናበቱ አይቀሬ በመሆኑም ከሪያድ በኩል እየቀረቡ የሚገኙ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚቀበሉ አይመስልም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በቀጣዩ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን አሸንፈው በዋይትሃውስ ለመቆየት የጋዛው ጦርነት መቆም ቢኖርበትም በኔታንያሁ ላይ ጫና አድርገው ጦርነቱን ማስቆም አልቻሉም።