ሄዝቦላህ በተለያዩ ጊዜያት በእስራኤል ጦር ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል
የእስራኤል ጦር አምስት ወታደሮቹ በደቡባዊ ሊባኖስ መገደላቸውን አስታወቀ።
ወታደሮቹ በደቡባዊ ሊባኖስ ከሄዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር በውጊያ ላይ እያሉ መሞታቸውን ነው የእስራኤል ጦር ያስታወቀው።
ይህንን ተከትሎም እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ ካስገባች ከመስከረም 20 ወዲህ የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ቁጥር 30 ደርሷል።
በሄዝቦላህ ላይ በአየር ድብደባ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው እስራኤል ካሳለፍነው መስከረም 20 ጀምሮ እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ በመላክ ውጊያ ጀምራች።
የሊበኖሱ ቡድን ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር በገጠመው ጦርነት በእስራኤል ጦር ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መሰንዘሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ የእስራኤል ወታደሮችን እንደገደለም አስታውቋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከእስራኤል የተከፈተበትን ጥቃት ለመመከትም አዲስ እና ሚስጥራዊ ወታደራዊ እዝ መመስረቱም ይታወሳል።
አዲሱ የሄዝቦላህ ወታራዊ እዝ ሮኬቶች እንዲተከሱ ትእዛዝ የሚሰጥ እና ከእስራኤል ጋር የእግረኛ ውጊያን የሚያከናውን መሆኑም ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያረጋገጡት።
ሄዝቦላህ አሁንም ቢሆን በርካታ መሳሪያዎች በእጁ እንዳለ የሚነገር ሲሆን፤ ከታጠቃቸው መሳሪያዎች መካልም ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያላዋላቸው አደገኛ ሚሳዔሎች ይገኙበታል ነው የተባለው።