እስራኤል ሀውቲዎች የሀማስ እና ሄዝቦላ እጣፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ስትል አስጠነቀቀች
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ሀውቲዎች የሚሳይል ጥቃት ካላቆሙ የሄዝቦላ እና የሀማስ እና የሶሪያው በሽር አላሳድ አይነት እጣፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል
የሀውቲ ጠቅላይ አብዩታዊ ኮሚቴ ኃላፊ ሞሀመድ አሊ አል-ሀውቲ ሀውቲዎች ማጥቃታቸውን እንደማያቆሙ ገልጿል
እስራኤል ሀውቲዎች የሀማስ እና ሄዝቦላ እጣፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ስትል አስጠነቀቀች።
በተባበሩት መንግስት ድርጅት(ተመድ) የእስራኤል አምባሳደር በኢራን የሚደገፉት ሀውቲዎች በእስራኤል ላይ እያደረሱ ያሉትን የሚሳይል ጥቃት ካላቆሙ የሄዝቦላ እና የሀማስ እና የሶሪያው በሽር አላሳድ አይነት እጣፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ሲሉ የመጨረሻ ያሉትን ማስጠንቀቂያ ትናንት አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ኢራንን ጨምሮ እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ የማትደርስበት ቦታ የለም ሲሉ ቴህራንንም አስጠንቅቀዋል። እስራኤል በኢራን አጋሮች የሚደርስባትን ጥቃት እንደማትታገስ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ነገርግን ከሰአታት በኋላ የእስራኤል ጦር ከየመን የተተኮሰ ሚሳይል ማክሸፉን አስታውቋል። ሀውቲዎች በቴልአቪቭ አቅራቢያ የሚገኘውን የቤን ጎሪዎን ኤየርፖርት እና በደቡባዊ እየሩሳሌም የሚገኝ የኃይል ጣቢያን በሃይፐርሶኒክ ሚሳይል እና በዙልፊቃር ባለስቲክ ሚሳይል በተከታታይ ኢላማ ማድረጋቸውን የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳርዔ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
እስራኤል ሚሳይል ማክሸፏን ማስታወቋን ተከትሎ የሀውቲ ጠቅላይ አብዩታዊ ኮሚቴ ኃላፊ ሞሀመድ አሊ አል-ሀውቲ ሀውቲዎች ማጥቃታቸውን እንደማያቆሙ ገልጿል።
"በእስራኤል ላይ የሚደረገው ድብደባ እና ለጋዛ የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል" ብሏል አሊ አል-ሀውቲ በኤክስ ገጹ።
ሀውቲዎች በእስራኤል የሚሳይል ጥቃት እያደረሱ ያሉት በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ዳኖን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እስራኤል ተጨማሪ የሀውቲ ጥቃቶችን መታገስ አትችልም ብለዋል።
" እናንተ ሀውቲዎች፣ ባለፈው አመት በመካከለኛው ምስራቅ ምን እንደተካሄደ ትኩረት አልሰጣችሁት ይሆናል"ያሉት አምባሳደሩ በሄዝቦላ፣ ሀማስ እና በአሳድ ላይ የደረሰውን አስታውሱ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
"ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው፤ ተመሳሳይ መጥፎ እጣፋንታ ይገጥማችኋል" ብለዋል ዳኖን።
ባለፈው ሳምንት እስራኤል ሰንዓን ጨምሮ የመን ውስጥ የሚገኙ በርካታ የሀውቲ ይዞታዎችን መምታቷን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል "ገና እየጀመረች ነው" የሚል ዛቻ አሰምተው ነበር።