ከስልጣን የታገዱት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን እንዲታሰሩ ፍርድ ቤት ወሰነ
ዩን በሀገሪቱ ታሪክ ስልጣን ላይ እያሉ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የመጀመሪያው መሪ ሆነዋል
ዩንን በመተካት ጊዜያዊ ፕሬዝደንት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ዱክ ሶ አብላጫ ቁጥር ተቃዋሚዎች ባሉበት ፖርላማ ታግደዋል
ከስልጣን የታገዱት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን እንዲታሰሩ ፍርድ ቤት ወሰነ።
የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት ወታደራዊ ህግ ማወጃቸውን ተከትሎ ከስልጣን የታገዱት ፕሬዝደንት ዩን እንዲታሰሩ በዛሬው እለት ፍቃድ መስጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩን በሀገሪቱ ታሪክ ስልጣን ላይ እያሉ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የመጀመሪያው መሪ ሆነዋል።
በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሙስና ምርመራ የሚያካሂደው ቢሮ (ሲአይኦ) የሴኡል ምዕራባዊ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ለአጭር ጊዜ የቆየውን የዩን ወታደራዊ ህግ እየመረመሩ ያሉ መርማሪዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ማጽደቁን አረጋግጧል።
ዩን አመጽ እንዲቀሰቀስ በማድረግ ተጠርጥረው ነው ምርመራ እየተካሄደባቸው የሚገኘው። ከስልጣን የመታገዳቸው ወይም "ኢምፒችመንት"ጉዳይ ለብቻው በሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።
በእስያ አህጉር በኢኮኖሚዋ አራተኛ እና የአሜሪካ ቁልፍ አጋር በሆነችው ደቡብ ኮሪያ አሁናዊ ፕሬዝደንት ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣት ያልተጠበቀ እና ቀውሱን የሚያባብስ ነው ተብሏል።
ዩንን በመተካት ጊዜያዊ ፕሬዝደንት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ዱክ ሶ አብላጫ ቁጥር ተቃዋሚዎች ባሉበት ፖርላማ ታግደዋል። የሀንን ከስልጣን መታገድ ተከትሎ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት የሆኑት የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቾይ ሳንግ ሞክ ለ179 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የእሁድ እለቱን የጄጁ ኤየር የበረራ ቁጥር 7C2216 አውሮፕላን መከስከስ አደጋ እየተከታተሉ ናቸው።
የወጣው የእስር ማዘዣ የሚያገለግለው እስከ ጥር 6፣2025 ሲሆን ተግባራዊ ሲደረግ ዩን በሴኡል የእስረኞች ማቆያ እንደሚገቡ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ የሀገሪቱን ዮን ሀፕ የዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ከስልጣን የታገዱት ፕሬዝደንት ጠበቃ ዩን ከብ-ኪዩን ግን ሲአይኦ ደቡብ ኮሪያ ህግ መሰረት ማዘዣ መጠየቅ አይችልም ሲል የእስር ማዘዣውን ውድቅ አድርጎታል።
ጠበቃው እንዳለው የፕሬዝደንቱ የህግ ቡድን ትዕዛዙ እንዲታገድ ለህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቱ አቤቱታ እንደሚያቀርብ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ዩን እንዲታሰሩ የፈቀደው ዩን ለጥያቄ ሲፈለጉ ያለአሳማኝ ምክንያት ሊቀሩ ስለሚችሉ እና ዩንን በወንጀል ለመጠርጠር መቂ ምክንያት በመኖሩ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
የእስር ትዕዛዙ መቼ እና እንዴት እንደሚፈጸም ግልጽ አይደለም።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንታዊ የጸጥታ አገልግሎት የእስር ማዘዣውን በህጉ መሰረት እንደሚያስፈጽም በዛሬው እለት ገልጿል። ሲአይኦ እንደገለጸው ፍርድ ቤቱ የፕሬዝደንቱ መኖሪያም እንዲፈተሽ ፍቃድ ሰጥቷል። ፖሊስ ከዚህ በፊት የፕሬዝደንቱን ቢሮ ለመፈተሽ ያደረገው ሙከራ በፕሬዝዳንታዊ ጸጥታ አገልግሎት ምክንያት ሳይሳካለት ቀርቷል።
ዩን ከታህሳስ 3፣2024 ጀምሮ መርማሪዎች ለጥያቄ እንደሚፈልጓቸው ቢጠይቋቸውም ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ሚዲያዎችን ሴንሰር ለማድረግ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማገድ የወጣውና ወዲያው የተሻረው ወታደራዊ ህግ በሀገሪቱ ከ 1980ዎቹ ወዲህ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።