እስራኤል በጋዛ መስጂድና ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ 24 ሰዎች ተገደሉ
በማዕከላዊ ጋዛ ዴር አል ባላህ በተፈጸመው የአየር ድብደባ 93 ሰዎች መቁሰላቸውም ተገልጿል
42 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ነገ አንደኛ አመቱን ይይዛል
እስራኤል በጋዛ በመስጂድ እና ትምህርት ቤት ላይ ኢላማ አድርጋ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ የ24 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
ጥቃቱ የተፈጸመው በማዕከላዊ ጋዛ ዴል አል ባላህ በአል አቅሳ ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኙ መስጂዶች እና ትምህርት ቤት ላይ ሲሆን 93 ሰዎች መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
መስጂዱ እና ትምህርት ቤቱ ተፈናቃዮች ተጠልለውባቸው የሚገኙ ናቸው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ “የሃማስ ሽብርተኞች ላይ የተጠና እርምጃ ወስጃለሁ” በሚል ጥቃት የተፈጸመባቸውን ስፍራዎች ቡድኑ የጦር ማዘዣ አድርጎ ሲጠቀምባቸው መቆየቱን ገልጿል።
በነገው እለት አንድ አመት የሚሞላው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ቴል አቪቭ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ሊባኖስ በማድረጓ በመጠኑ ጋብ ማለቱ ቢነገርም የአየር ድብደባው ግን ቀጥሏል።
የዛሬ ማለዳው ጥቃትም በእስራኤል ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያንን ቁጥር ወደ 42 ሺህ እንዲጠጋ ማድረጉ ነው የተገለጸው።
በሊባኖስ በስደት የሚኖሩ ፍልስጤማውያን በደቡባዊ ሊባኖስ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ለዳግም መፈናቀል በመዳረግ ላይ ናቸው።
ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለውና ጋዛን ያፈራረሰው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አንደኛ አመቱን ሲይዝ ተፋላሚዎቹ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በተለያዩ ሀገራት ሰልፎች እየተደረጉ ነው።
የፍልስጤሙን ሃማስና የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ትደግፋለች የምትባለው ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ትናንት በደማስቆ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ “በጋዛ እና በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እየሞከርን ነው” ብለዋል።
ሚኒስትሩ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው ሀገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ከቴህራን ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ግን ሀገራቸው ባለፈው ሳምንት በእስራኤል ላይ የወሰደችውን የሚሳኤል ጥቃት አወድሰው “ካስፈለገ በድጋሚ ልንፈጽመው እንችላለን” ማለታቸው ይታወሳል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም “እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት፤ (ለኢራን) ጥቃት ምላሽ መስጠታችን አይቀሬ ነው” ሲሉ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።