እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሱን ገለጸች
በሀገሪቱ የድንበር አቅራቢያ ወደ መኖሪያቸው እየተመለሱ የሚገኙ እስራኤላውያን ባሉበት እንዲቆዩ ታዘዋል
ሊባኖስ የእስራኤል ታንኮች በደቡባዊ ሊባኖስ ስድስት ስፍራዎች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን አስታውቃለች
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የደረሰችው የተኩስ አቁም ስምምነት እንደተጣሰ አስታወቀች፡፡
በሊባኖሱ ታጠቂ እና በቴልአቪቭ መካከል በአሜሪካ እና ፈረንሳይ አደራዳሪነት ተግባራዊ የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ከ14 ወራት በኋላ በሁለቱ ድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ የሀገራቱ ዜጎች ወደ መኖርያቸው እንዲመለሱ ይፈቅዳል፡፡
የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው የተኩስ አቁሙ የተጣሰው የሄዝቦላህ ታጣቂዎች እንደሆኑ የጠረጠራቸው ሰዎች በተለያዩ ተሸከርካሪዎች በደቡባዊ ዞን አቅራቢያ መታየታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሀሰን ፋድላላህ በበኩላቸው እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ወደሚገኘው መንደራቸው የሚመለሱ ሰዎችን አጥቅታለች ሲሉ ከሰዋል።
የሊባኖስ የደህንነት ምንጮች የእስራኤል ታንኮች በደቡባዊ ሊባኖስ በስድስት አካባቢዎች ላይ የእርሻ ቦታዎችን ጨምሮ ጥቃት መሰንዘራቸውን ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
የታንክ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት አካባቢዎች በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል ያለውን ድንበር ከሚያካልለው ሰማያዊ መስመር በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ።
በጥቃቱ ሁለት ንጹሀን መጎዳታቸው ሲነገር ሮይተርስ በአካባቢው ከሚገኙ የደህንነት ምንጮች አገኝሁት ባለው መረጃ የእስራኤል ወታደሮች አሁንም የሊባኖስ ድንበር ክልል ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በተኩስ አቁም ስምምነቱ የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ በ60 ቀናት ውስጥ የሚወጣ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች የማጥቃት ዘመቻ ላለማድረግ ተስማምተዋል
በትላንትናው ዕለት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ስምምነት በግጭት በተሞላው ቀጠና ውስጥ ግዙፍ የዲፕሎማሲ ስኬት ተደርጎ ቢወሰድም ምን ያህል ሊዘልቅ ይችላል የሚለው ግን ጥያቄ ውስጥ ይገኛል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰሜናዊ የእስራኤል ድንበር ለወራት ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ አዘዋል፡፡
ይህም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ መክተቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሄዝቦላህ በበኩሉ ተዋጊዎቹ የእስራኤልን ጥቃት ለመቋቋም ሙሉ በሙሉ ታጥቀው እንደሚቆዩ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ሙሉ ለሙሉ ለቆ እስኪወጣ ድረስ ታጣቂዎቹ ጣታቸውን ከቃታ ላይ ሳያነሱ በተጠንቀቅ ሁኔታዎችን እንዲከታተሉ አስጠንቅቋል፡፡