እስራኤል በሶሪያ የሚሳኤል ጥቃት ፈጸመች በሆምስ ከተማ የደረሰው ጥቃት የንብረት ውድመት ማስከተሉ ተነግሯል
ሶሪያ በበኩሏ እስራኤል የተኮሰሳቻቸውን በርካታ ሚሳኤሎች ማክሸፏን ገልጻለች
ሶሪያ በበኩሏ እስራኤል የተኮሰሳቻቸውን በርካታ ሚሳኤሎች ማክሸፏን ገልጻለች
እስራኤል በማዕከላዊ ሶሪያ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ።
ቴልአቪቭ ጥቃቱን የፈጸመችው ሶሪያ የተኮሰችው ጸረ አውሮፕላን ሚሳኤል ራሃት በተባለችው ግዛቷ በመውደቁ ነው ተብሏል።
ከሆምስ ከተማ አካባቢ የተተኮሰው መቃወሚያ አየር ላይ ተመቶ መውደቁን የእስራኤል ጦር ገልጿል።
እስራኤል ጸረ አውሮፕላን ሚሳኤሉ የተተኮሰበትን ስፍራ ኢላማ አድርጋ በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃትም የንብረት ጉዳት መድረሱ ነው የተነገረው።
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች የተኮሷቸው ሚሳኤሎች በሊባኖስ መዲና ቤሩት በኩል ስለማለፋቸው ሶሪያ ገልጻለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ መጠናቸውን ባይጠቅስም በርካታ የእስራኤል ሚሳኤሎችም ተመተው መውደቃቸውን ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አቪቼይ አድሬ ከሆምስ ባሻገር በሌሎች አካባቢዎችም ጥቃት መፈጸሙን የገለጹ ሲሆን፥ የደረሰ ጉዳት ግን የለም ብለዋል።
አየር ላይ ተመቶ ወድቋል ስለተባለው የሶሪያ ሚሳኤልም ሆነ ስለእስራኤል የአጻፋ ጥቃት ከሁለቱ ሀገራት መግለጫ ውጪ ከገለልተኝነት አካል ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል ሬውተርስ።
እስራኤል በሶሪያ የአውሮፕላን ማረፊያዎች እና የአየር ሃይል ጣቢያዎች ላይ ባለፉት ወራት ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
ጥቃቶቹም ኢራን በሶሪያ እና በሊባኖስ ለሚገኙ ታጣቂዎች የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማስተጓጎልን ኢላማ ያደረጉ ናቸው።
ቴህራን ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችው ሶሪያ ከፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጎን መሰለፏ ይታወቃል።