ፍርድ ቤትና ፖሊስ ግለሰቡ ላይ ለሰሩት ጥፋት ይቅርታ ጠይቀዋል
ባልደፈራቸው ሴቶች ምክንያት ለ15 ዓመታት የታሰረው ግለሰብ ከእስር ተለቀቀ፡፡
አሊ ቶሞሂ ይባላል፤ ከ15 ዐመት በፊት በፈረንጆቹ 1999 ላይ ከመኖሪያ ቤቱ ነበር በፖሊስ ተይዞ ወደ እስር ቤት የተወሰደው። ከታሰረበት ክፍል በፖሊስ እንዲወጣ የታዘዘው አሊ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅሎ እንዲቆም ይታዘዛል።
አምስት ሴቶችም እያለቀሱ የተደፈሩት በእሱ መሆኑን ለፖሊስ ሲናገሩ በአይኑ አይቷል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄ ለእልፍ ሌሊቶች መልስ ያጣ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ላይ የ72 ዓመት አዛውንት የሆነው አሊ በሰውነት ግንባታ ስፖርት ታዋቂ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ስፖርት ገፍቶበት ታዋቂ የመሆን ህልም እንደነበረውም ይናገራል።
የስፔኗ ካታሎኒያ ከተማ ነዋሪ የነበረው አሊ በአስገድዶ መደፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ መታሰሩን መቀበል ለእሱና ለቤተሰቦቹ ከባድ ነበር የሚለው አሊ ጉዳዩ ከራሱ አልፎ ለሴት ልጁም ህይወት ከባድ እንደነበርም አክሏል።
የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሴቶች ድርጊቱን አሊ እንደፈጸመባቸው መናገራቸው ብቻ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሊባል እንደቻለ ተገልጿል።
ይሁንና አሊ ከታሰረም በኋላ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የሚፈጸምባቸው ሴቶች መቀጠልን ተከትሎ ፖሊስ ብዙ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ፖሊስ ዘግይቶም ቢሆን ባደረገው ምርመራ ብዙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ይፈጽም የነበረ አንቶኒ ካርቦኔል የተባለ ሌላ ስፔናዊ እንደነበር ይደረስበታል።
ይህ ግለሰብ ከአሊ ጋር በመልክ መመሳሰላቸው የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሴቶች በስህተት አሊን ተጠያቂ አድርገውታል የተባለ ሲሆን ፖሊስም በወቅቱ ተጨማሪ ምርመራ አለማድረጉም ተጠቅሷል።
ከዚህ በፊት የአስገድዶ መደፈር ወንጀል በአሊ ተፈጽሞብናል ካሉ ሴቶች በተወሰደው ናሙና እና አሊ ከታሰረም በኋላ የተፈሩ ሴቶች ላይ በተወሰደ ናሙና መሰረት እውነተኛው ደፋሪ አንቶኒ ሆኖ በዘረመል ምርመራ ሊረጋገጥ ችሏል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ስህተት መስራቱን አምኖ ያለ ጥፋቱ ታስሮ የነበረው አሊ በመጨረሻም ንጹህ መሆኑ ተረጋግጦ ከእስር መፈታቱ ተገልጿል።