እስራኤላውያን ተቃዋሚዎች በፍልስጤማውያን ላይ በደል አድርሰዋል ለተባሉ ወታደሮች ድጋፋቸውን አሳዩ
ተቃዋሚዎቹ የእስራኤል ወታደሮች የተያዙበትን የሴድ ቴይማን የጦር ሰፈር ጥሰው ገብተዋል
የእስራኤል ወታደሮች በሴድ ቴይማን በታሰሩ የጋዛ ነዋሪዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸማቸው ተገልጿል
የእስራኤል ቀኝ ዘመን ተቃዋሚዎች በፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ በደል አድርሰዋል ተብለው ምርመራ ለተጀመረባቸው የእስራኤል ወታደሮች ድጋፋቸውን አሳዩ።
ተቃዋሚዎቹ ወታደሮቹ የሚገኙበትን ሴድ ቴይማን የተባለ የጦር ሰፈር በመውረር የተወሰኑት ጥሰው ገብተዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ከጋዛ የታፈሱ ፍልስጤማውያን ታሳሪዎችን ሲያሰቃዩ ነበር የተባሉትን ወታደሮች በቁጥጥር ስር ለማዋል ወደ ጦር ሰፈሩ ሲያመራም መንገድ በመዝጋት ለመከላከል ሞክረዋል።
“ጓደኞቻችን አንተዋቸውም በተለይ ለአሸባሪዎች” የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።
ተቃዋሚዎቹ በፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ በደል አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረው ለምርመራ የተወሰዱ ወታደሮች የሚገኙበትን ቤልቴድ ወታደራዊ ጣቢያን ጥሰው ለመግባት መሞከራቸውንም ነው ቢቢሲ የዘገበው።
አንዳንድ ወታደሮችም ሊይዟቸው በመጡ ፖሊሶች ላይ አይናቸውን የሚያቃጥል ነገር ሲረጩ ታይተዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ክስተቱን አጥብቀው የተቃወሙ ሲሆን፥ በሴድ ቴይማን ዙሪያ የታየው ሁከት እንዲረጋጋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት በወታደሮቹ ላይ የተጀመረው ምርመራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
“ቁጣ በበዛበት ወቅትም ቢሆን ህግ በሁሉም ላይ እኩል መፈጸም አለበት” ሲሉም ነው የተናገሩት።
የቀኝ ዘመሙ የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ግን ወታደሮቹን በቁጥጥር ስር ማዋል “አሳፋሪ እና እርባና ቢስ ነው” ብለውታል።
በደቡባዊ እስራኤል ቤርሻባ አቅራቢያ የሚገኘው ሴድ ቴይማን የጦር ሰፈር የጋዛ ታሳሪዎች ማሰቃያ ሆኗል የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ሲወጡ ሰንብተዋል።
የሃማስ ታጣቂዎች ናቸው በሚል ወደጦር ሰፈሩ የተጋዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አይናቸው ታስሮ ከቤት እንደማይወጡ ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳያመሩም ዳይፐር እንደሚደረግላቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሴድ ቴይማን የሚገኙ የህክምና ባለሙያ ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣም ባለፈው ወር በጦር ሰፈሩ የታሰሩ ሁለት ፍልስጤማውያን እግራቸው መቆረጡን መዘገቡ ይታወሳል።
በፍልስጤማውያኑ ታሳሪዎች ላይ የወሲባዊ ጥቃትና ድብደባ መፈጸሙን የሚያሳዩ ዘገባዎችም በተለያየ ጊዜ ቢወጡም የእስራኤል ጦር ክሶቹን አስተባብሏል።