የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በጋዛ ለቀጠለው ጦርነት ሃማስን ወቀሱ
ፕሬዝዳንቱ ከሀማስ ባለፈ አሜሪካ ለእስራኤል ያልተገደበ የጦር መሳርያ ድጋፋ በማድረግ ለጦርነቱ መቀጠል እጇ አለበት ብለዋል
ሃማስ ለመግለጫው በሰጠው ምላሽ “አባስ ከወራሪዎቻችን ጋር በአንድ ቦይ እንደሚፈሱ አመላካች ነው” ብሏል
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳነት ማህሙድ አባስ በጋዛ ለቀጠለው ጦርነት ሀማስን ተጠያቂ አደረጉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በጋዛ ለበርካታ ንጹሀን ሞት ምክንያት ለሆነው ጦርነት ቀዳሚ ተጠያቂዎቹ አሜሪካ እና እስራኤል ቢሆኑም ለጦርነቱ መቀጠል ሀላፊነቱን የሚወስደው ሃማስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በትላንትናው እለት እስራኤል የሀማሳን ወታደራዊ አዛዥ ሞሀመድ ዳይፍን ለመግደል ባደረገቸው የአየር ጥቃት 90 ንጹሀን ፍልስጤማውያን መሞታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የሀማስ ወታደራዊ አዛዥ ላይ አነጣጥሯል በተባለው የአየር ጥቃት አዛዡ ስለመገደሉ እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጥም ከሞቱን ንጹሀን ባለፈ 300 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡
እስራኤል በተቆጣጠረችው ዌስት ባንክ ውስን አስተዳደር ያላቸው አባስ በፕሬዝዳንታዊ ቢሯቸው በኩል ባወጡት መግለጫ “ሃማስ በጋዛ ለቀጠለው የዘር ማጥፋት ጦርነት የሞራል ፣ የህግ እና የፖለቲካ ተጠያቂነት አለበት” ብለዋል፡፡
በመግለጫው ዙርያ ሀሳቡን የሰጠው የሀማስ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሃላፊ ሳሚ አቡ ዙሀሪ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ ማህሙድ አባስ ከወራሪዎቻችን ጋር በአንድ ቦይ እንደሚፈሱ አመላካች ነው ብሏል፡፡
“መሰል የተዛባ ሀሳብ ፍልስጤማውያንን ከቅኝ ግዛት ለማውጣት የምናደርገውን ትግል የሚያደናቅፍ ሳይሆን ይልቁንስ ጠላቶቻችን መልካቸው በብርሀን እንዲታይ የሚስችል ነው” ሲል ገልጿል፡፡
ከ2007 ጀምሮ የጋዛን የባህር ዳርቻ አካባቢዎች ከአባስ ታማኞች በሀይል መንጠቅ የጀመረው ሃማስ በዛው አመት ሙሉ ለሙሉ ጋዛን ማስተዳደር ጀምሯል፡፡
በሀማስ ዘንድ “የእስራኤል ጉዳይ አስፈጻሚ” በሚል የሚጠሩት አባስ እና በታጣቂው ዘንድ ያለው ክፍተት እየሰፋ በሚገኝበት ወቅት የተሰጠው ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት በአካባቢው ያለውን የውስጥ ፖለቲካ ሽኩቻ የሚመላክት ነው ተብሏል፡፡
በአባስ ፣ ፋታህ እና ሃማስ መካከል ያለውን የፖለቲካ የበላይነት ሽኩቻ ለማሸማገል እና ወደ አንድነት እንዲመጡ የተለያዩ የአረብ ሀገራት መሪዎች በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡
ሌላኛው የሀማስ መሪ ባሲም ናይም “አባስ የአንድነት ስምምነት ላይ እንዳንደርስ ተጠያቂ ነው ይህ መሆኑ ደግሞ ለወራሪዎች እድል ከፍቷል” ሲል ተናግሯል፡፡
ፕሬዝዳነት አባስ ከእስራኤል ጋር ባላቸው ቅርርብ ምክንያት የተፈጠሩ ወንጀሎች በጋዛ ብቻ ሳይሆን በመላው ፍልስጤም የሚዳረስ ነው ሲልም ከሷል፡፡