የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ የኔታንያሁ አስተዳደር ለሄዝቦላህ ጥቃት "ያሻውን" ምላሽ እንዲሰጥ ፈቀደ
በጎላን ኮረብታዎች 12 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር ውጥረትን አባብሷል
ለሄዝቦላህ ድጋፍ የምታደርገው ኢራን በሊባኖስ ጦርነት እንዳይጀመር አስጠንቅቃለች
የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ የኔታንያሁ አስተዳደር ለሄዝቦላህ ጥቃት ምላሽ እንዲሰጥ ፈቀደ።
የአሜሪካ ጉብኝታቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ቴል አቪቭ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሀገሪቱ የደህንነት ካቢኔ ጋር መክረዋል።
በዚህም ካቢኔው የኔታንያሁ አስተዳደር እስራኤል በሀይል በተቆጣጠረችው የጎላን ኮረብታ የ12 ሰዎች ህይወትን ለቀጠፈው የሄዝቦላህ ጥቃት "በፈለገው መንገድና ጊዜ" እርምጃ እንዲወስድ መፍቀዱን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሊባኖሱ ቡድን ቅዴሜ እለት ለተፈፀመው ጥቃት ሃላፊነቱን እንደማይወስድ ቢገልፅም እስራኤልና አሜሪካ ሄዝቦላህ ጥቃቱን ማድረሱን አስታውቀዋል።
የእስራኤል የጦር ጄቶችም በትናንትናው እለት የቡድኑን ይዞታዎች ሲደበድቡ ውለዋል።
የምሽቱ የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ ውሳኔም በሄዝቦላህ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን በኩል የእስራኤልና ሄዝቦላህ ግጭት ወደለየለት ጦርነት እንዲያመራ እንደማትፈልግ ገልፃለች።
ግብፅ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር ውጥረት አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ ቴል አቪቭ የምትወስደው እርምጃ ቀጠናዊ ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል አመላክተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅትም እስራኤልም ሆነች ሄዝቦላህ ግጭት ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
እስራኤል ቅዳሜ ከወደ ደቡባዊ ሊባኖስ የተተኮሰው ሚሳኤል ኢራን ሰራሽ መሆኑን መግለጿ ይታወሳል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ 12 ሰዎች የሞቱበት ሚሳኤልን በተመለከተ ለቀረበው ክስ ምላሽ ሳይሰጥ እስራኤል በሊባኖስ ጦርነት ከመጀመር እንድትቆጠብ አሳስቧል።
ሶሪያም እስራኤል በሀይል በያዘችው የቀድሞ ግዛቷ (ጎላን ኮረብታዎች) ለተፈፀመው ጥቃት ተጠያቂዋ እስራኤል ናት የሚል መግለጫ አውጥታለች።