የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር በሀገሪቱ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች እንዲባረሩ ጥሪ አቀረቡ
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነትና የእስራኤል ፖሊስ ኤርትራውያን ስደተኞችን ለማባረር ከመግባባት ላይ ደርሰዋል
በቴል አቪቭ የሚኖሩ ኤርትራዉያውን ስደተኞች ጎራ ከፍለው መደባደባቸውን ተከትሎ 2 ሰዎች ሞተዋል
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጋቪር የእስራኤል መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን እንዲያባርር ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት ባሳለፍነው ቅዳሜ በቴል አቪቭ ከተማ ኤርትራውያን ስደተኞች ጎራ ላይተው እርስ በእርስ መደባደባቸውን ተከትሎ ነው።
በእስራኤል በሚኖሩ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካክል በተፈጠረው ግጭት ሁለት ሰዎች በደረሰባቸው ድብደባ መሞታቸው ሲረጋገጥ፤ አምስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት መድረሱም ተነግሯል።
በግጭቱ ላይ የተካፈሉት ኤርትራውያኑ በድንጋይ እና በዱላ እርስ በስርስ መደባደባቸውን ያስታወቀው ፖሊስ፤ በስፍራው የደረሱ የፖሊስ አባላት ግጭቱን ለማስቆም የማስጠንቀቂያ ተኩስ እስከ መተኮስ ድረስ መገደዳቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ቤን ጋቪር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “የእስራኤል ብሄረዊ ደህንነትና የእስራኤል ፖሊስ ኤርትራውያን ስደተኞችን ለማባረር ከመግባባት ላይ ደርሰዋል” ብሏል።
ሁለቱ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ከመግባባያው የደረሱት “ከአመት በፊት የቀረበውን ጥያቄ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ነው” እንደሆነም አስታውቋል።
“የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ጉዳዩን በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ፊት እንዲያቀርቡ እና የኤስራኤል ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ መግባባት ላይ ተደርሷል” ብሏል የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመግለጫው።
በአሁኑ ሰዓት በእስራኤል ውስጥ 20 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ አብዛኞቹ እርትራውያን ስደተኞች በደቡባዊ ቴል አቪቭ አካባቢ ነው በስፋት የሚኖሩት።
ኤርትራዉያን ስደተኞች ወደ እስራኤል የገቡት በፈረንጆቹ 2000 መጀመሪያ ላይ በግብጽ ድንበር በኩል አቋርጠው እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
የእስራኤል ነዋሪዎች በተለይም በደቡባዊ ቴል አቪቭ አካባቢ የሚኖሩ የሀገሪቱ ዜጎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በአካባቢ መኖራቸውን ተከትሎ የወንጀል እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ ነው ሲሉ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
በእስራኤል እንዲሁም በሌሎች ሀገራት በሚኖሩ በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል።
ከወር በፊት በእስራኤል ደቡባዊ ቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ተመሳሳይ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን እና አንድ ሰው ከፍኛ መቁሰሉን የታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ያመለክታል።
በእስራኤል የሚኖሩ ኤርትራውያን በተለያዩ ግዜያት እርስ በእርስ የሚጋጩ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ግንቦት ወር በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት አንድ ሰው በስለት ተወግቶ ጉዳት ደርሶበታል።
ባሳለፍነው መስከረም ወር በቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ከባድ ግጭት ደግሞ የእስራኤል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከ170 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፤ በወቅቱ የተከሰተው ግጭት የእስራኤልን መንግስት ማስቆጣቱ ይታወሳል።