እስራኤል በጋዛ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው - ኤል ሲሲ
የግብጹ ፕሬዝዳንት ከጀርመኑ አቻቸው ጋር በካይሮ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ሀገራት የጋዛው ጦርነት እንዲቆም ብርቱ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል
በጋዛ ከ500 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ለረሃብ መጋለጣቸው ተገልጿል
እስራኤል በጋዛው ጦርነት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው ሲሉ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ወቀሱ።
ፕሬዝዳንቱ ከጀርመኑ አቻቸው ፍራንክ ዋልተር ስቴንሜር ጋር በካይሮ ከመከሩ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኤልሲሲ በመግለጫቸው “ረሃብ በፍልስጤማውያን ላይ እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፤ እጅግ አሰቃቂ ነገር ነው፤ ጉዳዩ የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው” ብለዋል።
“ሁላችንም በፍልስጤማውያን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተመለከትን ቢሆንም ምንም ማድረግ አልቻልንም” ሲሉም ወቀሳቸውን አቅርበዋል ብሏል ዘ ናሽናል ኒውስ በዘገባው።
በቅርቡ 11ኛ ወሩን የደፈነው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ነዋሪዎች ያሏትን ጋዛ አፈራርሷ ከ96 በመቶ በላዩን ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋልጧል።
የህጻናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ቺልድረን) መረጃ እንደሚያሳየው 500 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ለከባድ ረሃብ ተጋልጠዋል።
እስራኤልና ሃማስን በማደራደሩ ሂደት ትልቅ ድርሻ የነበራት ግብጽ የጋዛውን ጦርነት የመቀጠል ፍላጎት አላቸው የሚሏቸውን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሲተቹ ቆይተዋል።
ረሃብን እንደጦር መሳሪያ መጠቀም በአለማቀፉ ህግ የተከለከለ ተግባር መሆኑን በመጥቀስም በፕሬዝዳንቷ በኩል ተቃውሞዋን ደጋግማ አሰምታለች።
ከፕሬዝዳንት ኤልሲሲ ጋር መግለጫ የሰጡት የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴንሜር፥ “በጋዛ ያለው አሰቃቂ ግጭት በፍጥነት ሊቆም ይገባል” ማለታቸው ተዘግቧል።
ካይሮ ተፋላሚ ሃይሎችን ለማደራደር የምታደርገውን ጥረት እንድትገፋበት በመጠየቅም አስከፊው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የእስራኤል አጋር የሆነችው በርሊን ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም እና ታጋቾች ማስለቀቂያ እቅድ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
ጀርመን ከግብጽ ዋነኛ የንግድ አጋሮች ውስጥ አንዷ ስትሆን በቢሊየን ዶላሮች የጋራ የትራንስፖርትና ኢነርጂ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ ነው። ካይሮ ከበርሊን ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንም ትገዛለች።
ኤልሲሲ ከጀርመኑ አቻቸው ጋር ሲመክሩ የአውሮፓ ሀገራት የጋዛው ጦርነት እንዲቆም ጠንካራ ጫና መፍጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል።