በእስራኤል በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በተከሰተ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገደሉ
በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በቴል አቪቭ በተከሰተው ግጭት 5 ሰዎች ተጎድተዋል
ግጭቱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካክል መከሰቱን የእስራኤል ፖለስ አስታውቋል
በእስራኤል ቴል አቪቭ በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የእስራኤል ፖሊስ አስታወቀ።
ትናንት ጠዋት በቴል አቪቭ በተከሰተው ግጭት ህይወታቸው ካለፈ ኤርትራውያን በተጨማሪ አምስት ሰዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል።
የእርስ በእርስ ግጭቱ በእስራኤል በሚኖሩ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካክል መከሰቱን የእስራኤል ፖለስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
በግጭቱ ላይ የተካፈሉት ኤርትራውያኑ በድንጋይ እና በዱላ እርስ በስርስ መደባደባቸውን ያስታወቀው ፖሊስ፤ በስፍራው የደረሱ የፖሊስ አባላት ግጭቱን ለማስቆም የማስጠንቀቂያ ተኩስ እስከ መተኮስ ድረስ መገደዳቸውን አስታውቋል።
ግጭቱ ወደተከሰተበት ስፍራ ያቀኑ የህክምና ቡድን ግጭቱ ወደ ነበረበት የቴል አቪቭ ማእከላዊ የአውቶብስ ጣቢያ አካባቢ ሲደርሱ እድሜያቸው በ30ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ሁለት ወንዶች በደረሰባቸው ከባድ ድብደባ ሞተው ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
በእሰረር በእርስ ግጭቱ 5 ኤርትራውያን ላይ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት ደርሷል ያሉት የህክምና ባለሙያዎቹ፤ ከእነዚህም ሁለት ሰዎች ከፍኛ መጎዳታቸውን፣ ሁለት ሰዎች መካከለኛ እንዲሁም አንድ ሰው ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ከወር በፊት በእስራኤል ደቡባዊ ቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ተመሳሳይ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን እና አንድ ሰው ከፍኛ መቁሰሉን የታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ያመለክታል።
በእስራኤል የሚኖሩ ኤርትራውያን በተለያዩ ግዜያት እርስ በእርስ የሚጋጩ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ግንቦት ወር በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት አንድ ሰው በስለት ተወግቶ ጉዳት ደርሶበታል።
ባሳለፍነው መስከረም ወር በቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ከባድ ግጭት ደግሞ የእስራኤል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከ170 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፤ በወቅቱ የተከሰተው ግጭት የእስራኤልን መንግስት ማስቆጣቱ ይታወሳል።
በእስራኤል ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያን እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።