እስራኤል የሶሪያን ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎች እንደምታወድም ገለጸች
እስራኤል በአመታት ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ጉልህ ክስተት በተስፋ እና በስጋት እየተከታተለችው ነው

የበሸር አላሰድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችል ችግርን ለመከላከል መሬት ላይ "ጥቂት ቁጥር" ወታደር ማሰማራቷን በዛሬው እለት ገልጻለች
እስራኤል የሶሪያን ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎች እንደምታወድም ገለጸች።
እስራእል በሶሪያ የዘመናዊ መሳሪያ ማዕከል ላይ የተጠናከረ ጥቃት እንደምትፈጽም እና የበሸር አላሰድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችል ችግርን ለመከላከል መሬት ላይ "ጥቂት ቁጥር" ወታደር ማሰማራቷን በዛሬው እለት ገልጻለች።
እስራኤል በአመታት ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ጉልህ ክስተት በተስፋ እና በስጋት እየተከታተለችው ነው።
የእስራኤል ቀንደኛ ተቀናቃኟ ኢራን ምሽግ አድርጋው የነበረው የአሳድ አገዛዝ ቢገረሰስም፣ ከአልቃ ኢዳ ጋር ግንኙነት የነበራቸው አማጺያን ፈጣን ግስጋሴ አደጋ ይኖረዋል የሚል ስጋት አላት።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የእስራኤል ጦር "የአየር መከላከያ ስርአቶችን፣ ከመሬት ወደ ሰማይ የሚተኮሱ ሚሳይሎችን፣ ከአየር ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳይሎችን፣ ክሩዝ ሚሳይሎችን፣ የረጅም ርቀት ሮኬቶችን እና የጠረፍ ሚሳይሎችን ጨምሮ በመላው ሶሪያ የሚገኙ ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎችን ያወድማል" ብለዋል።
አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን የአየር ጥቃቱ በመጭዎቹ ቀናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ሳአር ደግሞ እስራኤል በሶሪያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት እና የሚያሳስባት የዜጎቿን ደህንነት መጠበቅ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
"የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ወይም የረጅም ርቀት ሚሳይሎች እና ሮኬቶች በአክራሪዎች እጅ እንዳይገቡ ነው የምናጠቃው"ብለዋል ሳኣር።
በ2023 የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባደረሰባት ጥቃት አሁንም ቁጭት ውስጥ ያለችው እስራኤል ከጎረቤቷ ወደፊት ሊቃጣባት የሚችልን ስጋት ለመከላከል እየሰራች ነው።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት በድንበር አካባቢ የነበሩ ፈንጆችን በማጽዳት በቁጥጥሯ ስር ባደረገችው ጎላን ሀይት እና ከሶሪያ ጋር በሚያዋስናት ከጦርነት ነጻ በሆነው ቀጣና ላይ አዲስ ምሽግ ወይም "ባሪየር" አቋቁማለች።
የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት በለቀቀው ፎቶ የእስራኤል ኮማንዶ ጦር በሶሪያው የሄርሞን ተራራ ላይ ሰፍረው አሳይቷል።
ሳአር እንዳሉት የወታደሮቹ ስምሪት በጣም የተወሰነ ነው ብለዋል።
የሶሪያ አማጺያን ከ13 አመታት የእርስበርስ ጦርነት በኋላ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት ደማስቆን በመቆጣጠር፣ የበሸር አላሳድ አጋዛዝ እንዲያከትም አድርገዋል።