አሜሪካ በግዛቷ ለሚወለዱ ህጻናት ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውን ህግ ልትሽር ነው
ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ዜጎች ልጆቻቸውን በአሜሪካ ለመውለድ ወደ ቦታው እንደሚያመሩ ይታወሳል

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ለሚወለዱ ህጻናት ዜግነት እንዲሰጣቸው የሚፈቅደውን ህግ እንደሚሰርዙ ተናግረዋል
አሜሪካ በግዛቷ ለሚወለዱ ህጻናት ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውን ህግ ልትሽር ነው፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ባካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን መምረጧ ይታወሳል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጥር አጋማሽ ላይ ስልጣን እንደሚይዙ የሚጠበቅ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ከወዲሁ እነማንን እንደሚሾሙ ጨርሰዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የከረረ አቋም እንዳላቸው በተደጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን ህገ ወጥ ስደተኞችንም በሀይል እንደሚያባርሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን ደግሞ በአሜሪካ ለሚወለዱ ህጻናት ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውን ህግ እሽራለሁ ብለዋል፡፡
ሀገሩቱ በግዛቷ የሚወለዱ ህጻናት በቀጥታ የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ህግ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ ዜጎች በአሜሪካ ለመውለድ አስቀድመው ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡
ስደተኞች የአሜሪካዊያንን ጥቅም እየጎዱ ነው የሚል አቋም ያላቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ህግ እሰርዛለሁ፣ አሜሪካዊ ልጆች ያሏቸውንም ወላጆች አብሬ ወደመጡበት አባርራለሁ ሲሉም ዝተዋል፡፡
በአሜሪካ አምስት ሚሊዮን ዜጎች አሜሪካዊ ካልሆነ ስደተኛ ዜጎች የተወለዱ ሲሆን የዶናልድ ትራምፕ መመረጥን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች የመባረር ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡
በሀገሪቱ ከሚኖሩ ጠቅላላ ዜጎች ውስጥ 12 ሚሊዮን ያህሉ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደሚያባርሩ አሁንም በመናገር ላይ ናቸው፡፡