የሄዝቦላህ መሪ ለጥቂት ከግድያ ባመለጠበት የቤሩት ጥቃት እስራኤል 22 ሰዎችን ገደለች
የእስራኤል በማእከላዊ ቤሩት ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት አካባቢ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች
ሁለት የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር አባላት በደቡብ ሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት ምሽት በማእላዊ ቤሩት በፈጸመችው ጥቃት 22 ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
የሊባኖስ ባስልጣናት እንደተናገሩት ከሆነ የጥቃት ኢላማ የነበረው አንድ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ሲሆን፤ አመራሩ ለጥቂት ከግድያ ሙከራው ማምልጡን ሶስት የደህንነት ምንጮች አረጋግጠዋል።
የእስራኤል የአየር ድብደባ ኢላማ የነበረው ዋፊቅ ሳፋ የሄዝቦላህ ላይዘን እና የትብብር ክንፍ መሪ ሲሆን፤ የሄዝቦላህ እና የሊባኖስ መንግስት የደህንነት ተቋማት ግንኙነትን የማስተባበር ኃላፊነት ያለው ሰው ነው።
ዋፊቅ ሳፋ የትናንትናው የእስራኤል የአየር ድብደባ ዋነኛ ኢላማ የነበረ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ከግድያ ሙከራው ማምለጡን ነው የደህንነት ምንጮች ያረጋገጡት።
የእስራኤል የአየር ጥቃት ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት አፓርታማዎችና በርካታ ሱቆች የሚገኝበት ማእከላዊ ቤሩት ላይ በመፈጸሙ ነው በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት የደረሰው ተብሏል።
እስራኤል በስፍራው ላይ የአየር ድብደባ ከመፈጸሟ በፊት ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልሰጠችም ነው የተገለጸው።
ስለ አየር ድብደባው በእስራኤልም ይሁን በሄዝቦላህ በኩል እስካን የተባለ ነገር የለም።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በእስራኤል የማእከላዊ ቤሩት የአየር ድብደባ 22 ሰዎች ሲሞቱ 117 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።
በአየር ድብደባው ከሞቱ ሰዎች መካከል 8 የአንድ ቤተሰብ አባላት የሚገኙበት ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ሱስቱ ህጻናት እንደሆኑ እና በቅርቡ በደቡባዊ ሊባስ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ቤሩት በመምጣት መኖር የጀመሩ ናቸው።
በተያያዘ ዜና በሊባስኖ ውስጥ የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል በእስራኤል ጦር ጥቃት እንደተሰነዘረብት አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ዋና ማዘዣ ላይ ታንክ በመተኮሱ የጥበቃ ማማ ላይ የነበሩ ሁለት የሰላም አስከባሪ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የተገለጸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የሰላም አስከባሪ አባላት ደህንነት የአደጋ ተጋላጭነት ከእለት እለት እየጨመረ ነው ብሏል።