የሄዝቦላህ ባለስልጣናት ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ አስቀምጠውት የነበረውን ቅድመ ሁኔታ ሰረዙ
ከእስራኤል ጋር ለመደራደር በቅድሚያ በጋዛ የሚደረገው ጦርነት ሊቆም ይገባል ሲል ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ነው ሄዝቦላ እንደሰረዘ ያስታወቀው
ሄዝቦላህ የሊባኖስን እጣ ፈንታ ከጋዛ ጋር አያይዞ በሀገሪቷ ላይ የከፈ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጫና በርትቶበታል
ሄቦላህ ከእስራኤል ጋር ለመደራደር በጋዛ ተኩስ አቁም መደረግ አለበት በሚል አስቀምጦት የነበረውን ቅድመ ሁኔታ እንደተወው ተነግሯል፡፡
ቡድኑ ከባለፈው አመት ጥቅምት ሰባት ማግስት ጀምሮ ከሀማስ ጋር በመወገን በእስራኤል የሮኬት እና የሚሳኤል ጥቃት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ባለፈው አንድ አመት የጋዛ ጥቃት እስካልቆመ እና የተኩስ አቁም ስምምነት እስካልደተደረሰ ድረስ በቴልአቪቭ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚቀጥል ሄዝቦላህ ሲዝት መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ናይም ቃሲም በትላንትናው እለት በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ከሀማስ እና ከፍልስጤማውያን ጎን መቆማችንን ብንቀጥልም የሊባኖስ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ከእስራኤል ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለድርድር እንድንቀርብ ያቀረቡትን ሀሳብ እንቅበላለን ብለዋል፡፡
ምክትል መሪው ናይም ቃሲም “የፓርላማው አፈጉባኤው ናቢህ ቤሪ ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ሀሳብ ጠላታችን እስራኤል የምትቀበል ከሆነ ለመደራደር ዝግጁ ነን። በጦርነቱ የመቀጠል ፍላጎት ካላት ግን የውጊያ ውጤቶች ቀጣዩን ሁኔታ ይወስናሉ” ነው ያሉት፡፡
አፈ ጉባኤው ከሌሎች የሊባኖስ ፖለቲከኞች እና ከምእራባውያን ጋር በመነጋገር የተኩስ አቁም ተፈጻሚ እንዲሆን በቅርቡ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከሁለት ቀናት በፊት ሌሎች መካከለኛ የሄዝቦላህ አመራሮች በተመሳሳይ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ የመደራደር ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ የአቋም ለውጥ አድርጎ ይሆን የሚለው ሀሳብ በአካባቢው ከሚያመጣው የስትራቴጂ ለውጥ አንጻር ምላሽ የሚያሻው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡
የሀማስ ከፍተኛ ሀላፊ ሳሚ አቡ ዙሀሪ ሄዝቦላ ለሃማስ ያለው ድጋፍ እና የሚያንጸባርቀው አቋም በየትኛውም ሁኔታ እንደማይለወጥ ጠንካራ እምነት አለን ብለዋል፡፡
ሆኖም ሮይተርስ ስማቸውን ያለጠቀሳቸው የሊባኖስ ባለስልጣን እንደተናገሩት ሄዝቦላህ እየተጠናከረ የመጣውን የእስራኤል የአየር ላይ ጥቃት ተከትሎ የሚፈናቀሉ ሰዎች በመበርከታቸው እየታየ የሚገኝውን ህዝባዊ ጫና ለማቃለል ወደ ድርድር መቅረብን ዋነኛ አማራጭ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም እስራኤል በሊባኖስ የከፈተችው የምድር ውግያ ዘመቻ ቡድኑ ሚገኝበትን ወቅታዊ አቋም እንዲፈትሽ እንዳስገደደው ባለስልጣኑ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናት ሄዝቦላ የሊባኖስን እጣ ፈንታ ከጋዛ ጋር አያይዞ ሀገሪቱን የከፋ ጉዳት ውስጥ እንዳይከታት ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡