ሄዝቦላ በድንበር አካባቢ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሱን ገለጸ
ሄዝቦላ ይህን ያለው እስራኤል የተገደለውን የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህ ይተካሉ የተባሉ ሁለት የቡድኑ አባላትን መግደሏን ካሳወቀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው
የእስራኤል ጦር ትናንት እና ዛሬ በደቡብ ሊባኖስ በተካሄደው ውጊያ ሶስት ወታደሮች በጽኑ ቆስለዋል ብሏል
ሄዝቦላ በድንበር አካባቢ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሱን ገለጸ።
ሄዝቦላ በዛሬው እለት ላቦኔህ በምትባለው የሊባኖስ የድንበር መንደር አቅራቢያ በከባድ መሳሪያ እና በሮኬት በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።
ሄዝቦላ ይህን ያለው እስራኤል የተገደለውን የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህ ይተካሉ የተባሉ ሁለት የቡድኑ አባላትን መግደሏን ካሳወቀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በሰሜን እስራኤል የማስጠንቀቂያ ደዎሎች በዛሬው እለት ሲሰሙ እንደነበረ የገለጸው የእስራኤል ጦር ትናንት እና ዛሬ በደቡብ ሊባኖስ በተካሄደው ውጊያ ሶስት ወታደሮች በጽኑ ቆስለዋል ብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል የተገደለው የሄዝቦላ መሪ ሁለት ተተኪዎችን በትናንትናው እለት ገድላለች ብለዋል።
ኔታንያሁ ይህን የተናገሩት በከፍተኛ አዛዦች ግድያ ምክንያት በችግር ውስጥ የገባው ሄዝቦላ ምክትል መሪ በድርድር ተኩስ ለማቆም ከተስማማ ከሰአታት በኋላ ነው።
ኔታንያሁ "የሄዝቦላን አቅም አዳክመነዋል። ሀሰን ነሰረላህን እና ተተኪዎቹን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አሸባሪዎችን ደሞስስናል" ሲሉ ተናግረዋል። ነገርግን ኔታንያሁ ተገድለዋል ያሏቸውን ሁለት ተተኪዎች በሰም አልጠቀሱም።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት ነስረላህን ይተካል ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ሀሽም ሰይፈዲን ሳይወገድ አይቀርም ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሀጋሪ ቆየት ብለው የእስራኤል የጦር ጄቶች ባለፈው ሳምንት በሄዝቦላ የደህንነት ቢሮ ላይ ድብደባ በሚያካሄዱበት ወቅት ሀሽም ሰይፈዲን ውስጥ እንደነበር እስራኤል ታውቃለች ብለዋል።
የሰይፈዲን"ሁኔታ እየተጣራ ስለሆነ፣ ስናውቅ ለህዝብ እናሳውቃለን።"
ሰይፈዲን ከአየር ድብደባው በኋላ በአደባባይ አልታየም።
ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋር የሆነው ሄዝቦላ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የኢራን አጋር ከሆኑት ቡድኖች ውስጥ በጣም ጠንካራ የሚባለው ነው።
"ሄዝቦላ ከበርካታ አመታት ከነበረበት አንጻር ሳታይ ዛሬ ደክሟል" ብለዋል ኔታንያሁ።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት አንደገለጸው በደቡብ ሊባኖስ ከመሬት ስር በተሰሩ የሄዝቦላ ጣቢያዎች ላይ በተፈጸመው ከባድ የአየር ጥቃት ስድስት የዘርፍ አዛዦችን ጨምሮ 50 ተዋጊዎች ተገድለዋል። በአሁኑ ወቅት ያለው ቀጣናዊ ውጥረት ከአንድ አመት በፊት ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ነው።
የሄዝብላ መሪን መገደል እና የሊባኖስን ወረራ ለመበቀል ኢራን በእስራኤል ላይ በ180 ባለስቲክ ሚሳይል ጥቃት አድርሳለች።
የኢራንን ጥቃት ተከትሎ ኔታንያሁ "ኢራን ከባድ ስህተት ስርታለች፤ ዋጋ ትከፍላለች" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። ኔታንያሁ የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም የሚል ማስፈራሪያም አሰምተዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አርቃች በኢራን መሰረተልማት ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ከባድ ምላሽ እንደሚኖር አስጠንቅቀዋል።