እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ በፈጸመችው ጥቃት 33 ሰዎች ተገደሉ
የጋዛ የጤና ሚንስትር በመላው ጋዛ በትናንትናው እለት በደረሰ ጥቃት በአጠቃላይ 72 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል
በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍሊስጤማውያን ቁጥር 42 ሺህ 519 መድረሱ ተነግሯል
በጋዛ ከሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣብያዎች መካከል ትልቁ እንደሆነ በሚነገርለት ጃባሊያ በተፈጸመ ጥቃት 33 ሰዎች ሲገደሉ 85 ሰዎች መቁሰላቸው ተሰማ።
አንዳንድ ሰዎች በህንጻ ፍርስራሾች ውስጥ መያዛቸውን ተከትሎ በጥቃቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል።
የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ እንደተናገረው ከተገደሉት መካከል ህጻናት ይገኙበታል፤ እስራኤል በጥቃቱ ዙርያ እስካሁን ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠችም።
ከዚህ ጋር በተያዘ በትናንትናው እለት በሌሎች ስፍራዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች የ39 ሰዎች ህይወትን ሲነጥቁ በአጠቃላይ አርብ ዕለት በተለያዩ ጥቃቶች በመላው ጋዛ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 72 አድርሶታል።
የጃባሊያ ነዋሪዎች እንዳሉት የእስራኤል ታንኮች በከተማ ዳርቻዎች እና በመኖሪያ አካባቢዎች እየገፉ መጥተው በካምፑ ማዕከላዊ ስፍራ ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም የእስራኤል ጦር በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ቤቶችን ከአየር እና ከመሬት በሚፈጽመው ጥቃት እያወደመ ፤ እንዲሁም ቦምቦችን በህንፃዎች ውስጥ በማስቀመጥ ከርቀት እያፈነዳ ነው ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በጃባሊያ ሲንቀሳቀስ የቆየው የእስራኤል ጦር ሃሙስ እለት በፈጸማቸው የአየር ላይ ጥቃቶች በደርዘን የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን መግደሉን እና ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ማፈራረሱን ገልጿል።
ጦሩ በጃባሊያ የሚደርገው ዘመቻ የሃመስ ታጣቂዎች ለውግያ ድጋሚ እንዳይደራጁ አቅማቸውን መበታተን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግሯል።
የአካባቢው ባለስልጣናት በበኩላቸው በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ፣ ሃኑን እና ቤትላሂያ መንደሮች ላይ ከፍተኛ ውግያ እያደረጉ መሆናቸውን ተከትሎ የኢንተርኔት እና የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው የነፍስ አድን ስራዎችን አዳጋች እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
እስራኤል ባሳለፍነው ሁለት ሳምንት በጋዛ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የሞቱ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ወደ 42 ሺህ 519 ማሻቀቡን በሃስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በእስራኤል ድብደባ የቆሰሉ ፍሊስጤማውያን ቁጥር 99 ሺህ 637 የደረሰ ሲሆን፤ ከ10 ሺህ በላይ ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ነው የተባለው።