የሀማስ መሪ መገደል የጋዛውን ጦርነት አያስቆመውም - ኔታንያሁ
የመሪውን ግድያ ያረጋገጠው ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደረስ ታጋቾችን እንደማይለቅ ገልጿል
ምዕራባውያን የያህያ ሲንዋር ግድያ በጋዛ ሰላም እንዲሰፍን እድል እንደሚሰጥ እየገለጹ ነው
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ እና ሊባኖስ የሚካሄደው ጦርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዛቱ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ የጦርነቱን ቀጠይነት አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ግድያ በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ለማስቆም ይረዳል በሚል የተያዘውን ተስፋ ውሀ ቸልሶበታል፡፡
ኔታንያሁ የሲንዋርን ግድያ “የማዕዘን ዲንጋይ ነው” ብለው ቢጠሩትም በቅርብ ሳምንታት በጋዛ እና በደቡባዊ ሊባኖስ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ የሚገኘው ዘመቻ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል ፡፡
“በቀጠናው በኢራን የሚደገፉ በየመን ፣ ሶርያ ፣ ሊባኖስ ፣ በኢራቅ እና ጋዛ የሚገኙ ክፉ እጆችን ለማስቆም ጥሩ አጋጣሚ አግኝተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ይህን ከማሳካት እና የህዝባችንን ደህንነት ከማረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ኔታንያሁ ታጋቾች ሳይለቀቁ በጋዛ ጦርነት አይቆምም ቢሉም የመሪውን ግድያ ያረጋገጠው ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደረስ ታጋቾችን እንደማይለቅ ገልጿል።
የቡድኑ ምክትል መሪ ከህሊል አል-ሃያ ዛሬ ከስአት በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ ያህያ ሲንዋር “እስራኤልን እየተዋጋ ነው የሞተው” ብለዋል።
“ያህያ ሲንዋር የሞተው ወደፊት እየገሰገሰ እንጂ እያፈገፈገ አይደለም፤ መሳሪያውን ታጥቆ ጦሩን ከፊት ሆኖ እየመራ በሁሉም የውጊያ ቦታዎች ወራሪ ኃይሎችን እየተጋፈጠ ነው የተገደለው” ብለዋል የሃማስ ምክትል መሪ በመግለጫቸው።
የሃማስ አጋር የሆነው የሊባኖሱ ሄዝቦላህም በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዛተ ሲሆን ኢራን በበኩሏ የሲንዋር ግድያ የፍልስጤማውያንን የትግል መንፈስ የሚያጠናክር ነው ብላለች፡፡
የኔታንያሁ አስተያየት የሲንዋር ግድያ በቀጠናው ጦርነትን ለማስቆም ያግዛል በሚል ተስፋ ያደረጉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ ከምዕራባውያን መሪዎች ሀሳብ ጋር ተቃርኖ ያለው ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስርቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር “ምንም እንኳን ያህያ ሲንዋርን የሚተካው ሰው የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው ባናውቅም፤ ታጋቾችን ለማስመለስ እና ጦርነቱን ለማስቆም እንቅፋት ሆኖ የሰነበተው ዋነኛ ሰው ተወግዷል፤ አሁን መተኮር ያለበት የተኩስ አቁም ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነው” ብለዋል፡፡
የእስራኤል ዋና ደጋፊ አሜሪካ ከሃማስ እና ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ለወራት ያደረጋቻቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡
እስራኤል በሳምንታት ልዩነት ውስጥ ከፍተኛ የሀማስ እና ሄዝቦላህ መሪዎችን በመግደል ኢራን ለአስርተ አመታት ስትደግፋቸው የነበሩ ቡድኖችን አቅም እያዳከመች እንደምትገኝ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡