በአሜሪካ እና በእስራኤል “ግትርነት” ምክንያት የጋዛ ጦርነት ቀጥሏል - ሩስያ
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ አሜሪካ ለእስራኤል 17.9 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳርያ ድጋፍ አድርጋለች
የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ፍልስጤማውያን የራሳቸውን እድል እንዲወስኑ ዋስትና ሊሰጡ እንደሚገባም ሩስያ ጠይቃለች
የጋዛ ጦርነት እስካሁን እንዲቀጥል የእስራኤል እና አሜሪካ “ግትርነት” ዋና ምክንያት እንደሆነ ሩስያ አስታውቃለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “አስከፊውን የጥቃት አዙሪት እንዳያስቆም እንቅፋት ሆነዋል” ሲሉ በተመድ የሩስያ ተወካይ ተናግረዋል።
አንድ አመት በሞላው የጋዛው ጦርነት ዙርያ የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ነው የሩስያ ተወካይ ቫስሊ ኔቤንዚያ ይህን ያሉት፡፡
ተወካዩ፤ “የጥቅምት ሰባቱ የሀማስ ጥቃት አሳዛኝ አጋጣሚ ነው ነገር ግን እስካሁን በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ለሚገኘው ምህረት የለሽ እና ኢሰብአዊ የጅምላ ቅጣት በምክንያትነት መቅረቡ ፍትሀዊ አይደለም” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የጋዛ ነዋሪዎች ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የሰብአዊ ቀውስ እንዲያስተናግዱ ተገደዋል ሲሉ ነው የወቀሱት፡፡
ኔቤንዚያ በእስራኤል የአየር እና የምድር ዘመቻ ምክንያት ባለፈው አመት ወደ 42,000 የሚጠጉ ሰዎች ፤ በተለይም ሴቶች እና ህጻናት በጋዛ መገደላቸውን ገልጸው ፤ የቆሰሉት እና የጠፉ ሰዎች ቁጥር ወደ 100 ሺህ መቃረቡን አብራርተዋል።
ጦርነቱ 2 ሚሊየን ፍልስጤማውያንን ከቀያቸው ከቀያቸው ቢያፈናቅልም ዋሽንግተን እና ቴልአቪቭ ምንም ድንጋጤ አለማሳየታቸው ተቀባይነት እንደሌለውም ነው ያነሱት።
የንጹሀን ግድያ እና ስቃይ እንዲቀጥል የእስራኤል አመራር “ግትርነት” እና የአሜሪካ መተባበር የፀጥታው ምክር ቤት ይህን አስከፊ ጦርነት እንዳያስቆም እንቅፋት በመሆናቸው ሰቆቃው እንዲቀጥል አድርጓል ሲሉ በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
ዋሽንግተን ከመጋቢት በፊት 2024 በፊት በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቁ በርካታ የጸጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቦችን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓ ይታወቃል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዋትሰን ኢንስቲትዩት ባወጣው ሪፖርት መሰረት አሜሪካ ባለፈው አመት ለእስራኤል 17.9 ቢሊዮን ዶላር በክብረ ወሰን የተመዘገበ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥታለች።
የመድፍ ተተኳሾች ፣ ጥይቶች እና 907 ኪሎግራም የሚመዝኑ ቦንቦች ከዋና ዋና የጦር መሳርያ ድጋፍ አይነቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
የሩሲያው ዲፕሎማት በጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ የሚገኘው የጸጥታ ሁኔታ መፍትሄ የሚበጅለት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ እውነተኛ የሆነ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አደራዳሪ ቡድን ሊሳተፍበት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም "የጋራ ግባችን የፀጥታው ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ መላውን መካከለኛው ምስራቅ ሊያዳርስ የሚችለውን ደም መፋሰስ ማስቆም ነው" ብለዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት አባላትም ፍልስጤማውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ህጋዊ መብት በተግባር ላይ እንዲውል ዋስትና ሊሰጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡