ሀማስ ከጋዛ ውጪ ከሚገኙ አባላቱ አዲስ መሪ ለመሾም እየተመካከረ ነው
የሞቱ መሪዎቹን በፍጥነት የመተካት ልምድ ያለው ሀማስ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል በሆነው የሹራ ካውንስል አዲስ መሪ እንደሚሾም ይጠበቃል
የሟቹ ያህያ ሲንዋር ወንድም ሞሀመድ ሲንዋር በጋዛ ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ውግያ በማስተባበር እና በመምራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ግምት አግኝቷል
ከሰሞኑ መሪው የተገደለበት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሀማስ ከጋዛ ውጭ ከሚገኙ አባላቶቹ አዲስ መሪ ለመሾም እየመከረ እንደሚገኝ ተነገረ።
የቡድኑ መሪ ያህያ ሲንዋር ከእስራኤል ጦር ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ባሳለፍነው እሮብ መሞቱ ተነግሯል።
ይህን ተከትሎም ከሶስት ወራተር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እስራኤል የሀማስ ከፍተኛ ሀላፊን ስትገድል ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
እስማኤል ሀኒየህ በተሄራን መገደሉን ተከትሎ ሲንዋር የፖለቲካ እና ወታደራዊ ክንፉን በጋራ ሲመራ ቆይቷል።
መሀመድ ሲንዋር የያህያ ሲንዋር ወንድም በጋዛ ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ውግያ በማስተባበር እና በመምራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡
ሀማስ በአመራር ምርጫ ውይይቶቹ ላይ የዋነኛ አጋሩን ኢራንን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፤ የፖሊቲ ቢሮ አባላቶቹ መሸሸጊያ የሆነችው የባህረ ሰላጤው ሀገር ኳታርንም ሀሳብ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አንድ አመትን በተሻገረው ጦርነት ከፍተኛ የተባለው የእስራኤል ጦር ሁለገብ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ የሀማስ ታጣቂዎችን እና በጋዛ እና ከጋዛ ውጪ የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናቶቹን ህይወት አሳጥቷል።
ተተኪ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰበው የሲንዋር ምክትል ካሊል አል-ሃይያ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እስካልወጡ እና ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ የእስራኤል ታጋቾች አይመለሱም ሲሉ አርብ ዕለት ጠንከር ያለ ሀሳብ ሰንዝረዋል።
የሃማስ ዋና ተደራዳሪ ከሆነው ካሊል አልሃያ በተጨማሪ ሀማስን በመሪነት ሊረከቡ ይችላሉ ተብሎ የተጠቀሱት ሌሎች ዋና ዋና የአመራር ተፎካካሪዎች መካከል ከእስማኤል ሀኒየህ በፊት የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ የነበሩት ኻሊድ መሻል እና የሹራ ካውንስል ሊቀመንበር መሀመድ ዳርዊሽ ተጠባቂ ናቸው።
ሃማስ የሞቱ መሪዎቹን በፍጥነት የመተካት ታሪክ ያለው ሲሆን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል የሆነው የሹራ ካውንስል አዲስ መሪ የመሾም ሃላፊነት ተሰጥቶታል።
የሹራ ካውንስል በጋዛ ሰርጥ፣ በዌስት ባንክ፣ በእስራኤል እስር ቤቶች እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የፍልስጤም ዲያስፖራ ተወካዮችን እና ሁሉንም የሃማስ አባላትን ይወክላል፤ አዲስ የሚመረጠው መሪም በጋዛ ባይሆንም የተኩስ አቁም ንግግር ለማስጀመር እና ለመወሰን ስልጣን የሚኖረው ነው።
ሃማስ ውሳኔውን ሲወስን ለቡድኑ አባላት መጠለያ ሆና ለአመታት ለዘቀችው እና በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረት እያደረገች ለምትገኝው ኳታር ማሳወቅ ይኖርበታል።
ቡድኑን ለአመታት በትጥቅ እና ገንዘብ ስትደግፍ የቆየችው ኢራን በቀጣዩ መሪ ላይ የሚኖራት ይሁንታ ደግሞ ምርጫውን የሚያጸና ቡራኬ ይሆናል።