በ2006ቱ የአለም ዋንጫ ስሙ መግነን የጀመረው ቡፎን ከአዙሪዎቹ ጋር የአለም ዋንጫን አንስቷል
የአለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂዎች ስም ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን ከሚመጡት መካከል አንዱ የሆነው ጂያንሉጂ ቡፎን በ45 አመቱ ጓንት መስቀሉን አስታውቋል።
ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ የእግር ኳስ ህይወቱን አሃዱ ባለበትና ዳግም በተመለሰበት የሴሪቢ ክለቡ ፓርማ ነው ስንብቱን ይፋ ያደረገው።
ቡፎን በኢንስታግራም ገጹ ላይ “ሁሉንም ነገር ሰጥታችሁኛል፤ እኔም ያለኝን አልነፈግኳችሁም፤ የጋራ ጥረታችንም ስኬታማ ነበር” ሲል አስፍሯል።
የጂያሉጂ ቡፎን አስደናቂ ችሎታ የተገለጠው ጀርመን ባስተናገደችው የ2006ቱ የአለም ዋንጫ ነው።
አዙሪዎቹ ፈረንሳይን በመለያ ምት አሸንፈው ዋንጫ ባነሱበት በዚህ ውድድር ቡፎን ሁለት ብቻ ጎሎች ተቆጥረውበታል (በክለብ አጋሩ ክርስቲያን ዛካርዶ እና ዜነዲን ዚዳን በፍጻሜው ያስቆጠረበት የፍጹም ቅጥት ምት)።
ዚዳን ማርኮ ማታራዚን በቴስታ መትቶ በቀይ ካርድ በወጣበት የበርሊኑ የፍጻሜ ፍልሚያ ቡፎን የዚዳንን ተደጋጋሚ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አክሽፏል።
ቡፎን ጁቬንቱስ 10 የሴሪአ ዋንጫዎችን ሲያነሳም የኋላ ደጀን ነበር።
አሮጊቶቹ በ”ካልቾፖሊ” የእግርኳስ ቅሌት ወደ ሴሪቢው ሲወርዱ ያልተለያቸው ጂያሉጂ ቡፎን ቢያንኮነሪዎቹ (ነጭ እና ጥቁር ለባሾቹ) ወደ አንደኛው ዲቪዚዮን ሲመለሱም ግባቸውን ሳያስደፍር ለስኬት አብቅቷቸዋል።
በ”ካልቾፖሊ” ቅሌት ቡፎን እና ጁቬንቱስ ሁለት የሴሪአ ዋንጫዎችን መቀማታቸው ይታወሳል።
ጁቬንቱስ የቡፎንን ስንብት አስመልክቶ “ያዳንካቸው ድንቅ ሙከራዎች፣ ፈገግታ እና ጸባይህ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል፤ እናመሰግናለን” የሚል መልዕክት በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
ቡፎን ለሶስት አስርት ገደማ በተለያዩ ክለቦች ሲያሳልፍ ሊሳካለት ያልቻለው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ነው።
ከጁቬንቱስ ጋር ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫ አላነሳም፤ በ2013 በኤሲ ሚላን፣ በ2015 በባርሴሎና እንዲሁም በ2017 በሪያል ማድሪድ ተሸንፈው ዋንጫውን ሳይስም ቀርቷል።
በ2018 ከጁቬንቱስ ወደ ፓሪስ ሴንት ጀርሜን ያመራው ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ከአንድ አመት በኋላ የሀገሩን ክለብ ቱሪን መቀላቀሉ አይዘነጋም።
በ2021ም የእግርኳስ ህይወቱን ወደጀመረበት ፓርማ የተመለሰ ሲሆን፥ የአንድ አመት ኮንትራት እያለው ትናንት ከእንግዲህ በእግርኳስ መረብ ኳስ ሳድን አትመለከቱኝም ብሏል።