ቤልጂየማዊው ግብ ጠባቂ ፍጹም ቅጣት ምት ባደነ በደቂቃዎች ውስጥ ህይወቱ አልፏል
የ25 አመቱ ግብ ጠባቂ አርኔ ኢስፔል ህይወቱ ያለፈበት ምክንያት ግን አልተገለጸም
ዊንክል ስፖርት ቢ ለተሰኘው ክለብ የሚጫወተው ኢስፔል በቤልጂየም ታዋቂ ግብ ጠባቂ ነው ተብሏል
የቤልጂየም ሁለተኛ ሊግ በዚህ ሳምንት ያልተጠበቀ ክስተት አስተናግዷል።
ዊንክል ስፖርት ቢ እና ዌስትሮዜቤክ የተሰኙት ክለቦች ጨዋታቸውን እያደረጉ እያለ የዊንክል ስፖርት ቢ ግብ ጠባቂ ተዝለፍልፎ ወድቋል።
2 ለ 1 እየተመራ የነበረው ዌስትሮዜቤክ በሁለተኛው አጋማሽ አቻ የሚሆንበትን እድል የሚፈጥር የፍጹም ቅጣት ምት ያገኛል።
የዊንክል ስፖርት ቢ ግብ ጠባቂው አርኔ ኢስፔል ግን ይህን እድል ያመክንባቸዋል።
ከዚህ ተጋድሎው ከሰከንዶች በኋላ ነው ግብ ጠባቂው የወደቀው።
የቡድኑ የህክምና ቡድን አባላትም ተረባርበው ህይወቱን ለማትረፍ ቢሞክሩም ሆስፒታል እንደደረሰ መሞቱ ተነግሯል።
የ25 አመቱ ግብ ጠባቂ በቤልጂየማውያን ዘንድ ተወዳጅና ታዋቂ መሆኑ የተነገረለት ሲሆን፥ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ማለፉ የስፖርት ቤተሰቡን አሳዝኗል ብሏል ዴይሊ ሜል በዘገባው።
የኢስፔል ህልፈት ምክንያት ግን እስካሁን ምን እንደሆነ አልተገለጸም።
“ግብ ጠባቂው የፍጹም ቅጣት ምቱን አድኖ ክለቡ መሪነቱ እንዲያስጠብቅ ማድረጉ የፈጠረው ደስታ ሳይበርድ ወዲያውኑ መውደቁና ከጥቂት ቆይታ በኋላም ህይወቱ አለፈ መባሉን አሁንም ድረስ ለማመን ይከብዳል” ብሏል ክለቡ ባወጣው መግለጫ።
የክለቡ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ፓትሪክ ሮትሴራትም ፥ “አርኔ ኢስፔል ሙሉ ጊዜውን ለዊንክል ስፖርት የሰጠ ነው፤ በክለብ አጋሮችም ሆነ ደጋፊዎችም እጅግ የተወደደ ግብ ጠባቂ ነው፤ የህልፈቱ ዜና ትልቅ አስደንግጦናል” ነው ያሉት።
ክለቡ፣ ደጋፊዎች እና የኢስፔል ቤተሰቦችም ተወዳጁን ግብ ጠባቂ ለመዘከር በሲንት ኢሎይስ ዊንክል ጎዳና የእግር ጉዞ ማድረጋቸው ተገልጿል።