ህንድ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ መግዛት እንድታቆም አሜሪካ ጠየቀች
የአሜሪካ ወዳጅ ሀገራት ከሩሲያ መሳሪያ ባለመግዛት ራሳቸውን ከማዕቀብ ሊታደጉ እንደሚገባ ዋሺንግተን አስጠንቅቃለች
ህንድ የመሳሪያ አቅርቦቶችን ከየት ማገግኘት እንዳለብኝ የመምረጥ መብቱ እንዳላት አስታውቃለች
የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎልውድ አውስቲን ህንድ ከሩሲያ ለመግዛት ባቀደችው ኤስ-400 የአየር መቃወሚያ የጦር መሳሪያ ዙሪያ ከህንድ አቻቸው ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም የአሜሪካ አጋር ሀገራት ከሩሲያ የጦር መሳሪያያ ከመግዛት እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ሎልውድ አውስቲን “የአሜሪካ ወዳጅ ሀገራት እና አጋሮች ራሳቸውን ከሩሲያ ሰራሽ የጦር መሳሪያ እንዲያርቁ አሳስበናል፤ እንዲህ በማድረግም ከአሜሪካ ሊጣልባቸው ከሚችል ማዕቀብ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል” ብለዋል።
ህንድ እስካሁን ኤስ-400 የተባለውን መሳሪያ ከሩሲያ ስላልተረከበች ማዕቀብ እንደማይጣልባት ማስታወቃቸውንም ሮይተርስ ዝግቧል። ህንድ ከሩሲያ ጋር የገባችውን የ5.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሳይል ሲስተም ግዢ እንድትሰርዝም የትራምፕ አስተዳደር ጠይቋል፡፡
ህንድ በበኩሏ የመሳሪያ አቅርቦቶችን ከየት ማገግኘት እንዳለብኝ የመምረጥ መብቱ እንዳላት አስታውቃለች፡፡ ይህም ለኒውዴልሂ ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር የመጀመሪያ የውዝግብ ነጥብ እንደሚሆንባት ተገልጿል፡፡
“ህንድ እና አሜሪካ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አላቸው፡፡ ህንድ ከሩሲያ ጋር ደግሞ ልዩ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶች አሏት” ሲሉ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኑራግ ስሪቫስታቫ ስለታሰበው የኤስ-400 ግዢ ተናግረዋል ፡፡
“ህንድ ሁል ጊዜም ገለልተኛ የውጭ ፖሊሲን ተከትላለች” ያሉት ቃል አቀባዩ “ይህ በብሔራዊ ደህንነት ጥቅማችን የሚመራውን የመከላከያ ግኝቶቻች አቅርቦቶቻችንንም ይመለከታል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቱርክ ባሳለፍነው ዓመት ከሩሲያ S400 የተባለውን መሳሪያ በመግዛቷ ከአሜሪካ ማዕቀብ እንደተጣለባት አይዘነጋም።
ህንድ ለኤስ-400 መሳሪያ ግዢ እ.ኤ.አ. በ2019 ፣ 800 ሚሊዮን ዶላር ለሩሲያ የከፈለች ሲሆን፣ የመሳሪያዎች ባትሪዎች በያዝው ዓመት ህንድ እንደሚገቡ ይጠበቃል።