ባይደን “ፑቲን ገዳይ ነው” ማለታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ይቅርታ እንድትጠይቅ ሩሲያ አሳሰበች
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሩሲያው አቻቸውን በአሜካ ምርጫ ጣልቃ መግባታቸው ዋጋ ያስከፍላቸዋልም ብለዋል
የባይደንን ንግግር “መጥፎ” ያለችው ሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደሯን ልትጠራ ነው
“ፑቲን ገዳይ ነው” የሚለውን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት የጆ ባይደንን ንግግር ያወገዘችው ሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደሯን ለምክክር ልትጠራ እንደሆነ አስታወቀች፡፡
የባይደንን ንግግር በ“መጥፎ”ነት የፈረጀችው ሞስኮ ከዋሽንግተን ጋር ያላትን ግንኙነት ልታጤነው እንደምትችል አስታውቃለች፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባዩ ዲሜትሪ ፔስኮቭ “የሃገራቱ ግንኙነት እንዲሻሻል አልፈለጉም” በሚል ባይደንን ወቅሰዋል፡፡
ሃገራቸው “ተመጣጣኝ እርምጃ”ን ልትወስድ እንደምትችልም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
የሩሲያ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ቆንስጣንጢን ቆሳሼቭ በበኩላቸው አሜሪካ “በንግግሩ ላይ ማብራሪያ የማትሰጥና ይቅርታ የማትጠይቅ ከሆነ አምባሳደር መጥራቱ ብቻ በቂ አይደለም” ብለዋል፡፡
አምባሳደር የመጥራቱን ውሳኔ ለጋዜጠኞች ያሳወቁት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ በበኩላቸው ለሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት መሻከር አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ሃገራቸውን ከእንዲህ ዐይነቱ የአሜሪካ አካሄድ ለመከላከል እንደሚገደዱም ነው ቃል አቀባይዋ የተናገሩት፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ካሸነፉት የ2020ው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ስለ ሩሲያ ጣልቃ ገብነት የተጠየቁት ባይደን “ፑቲን ዋጋ ይከፍላል” ያሉ ሲሆን “ውጤቱንም በቅርቡ ታያላችሁ” ሲሉም ተናግረዋል።