ሩሲያን ጨምሮ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው 16 ሃገራት የመንግስታቱ ድርጅት እንዲያግዛቸው ጠየቁ
ትራምፕ ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ሃገራት ላይ ማዕቀብ መጣላቸው የሚታወስ ነው
ሃገራቱ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነው ማዕቀቡ የተጣለባቸው
ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ በአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ የተጣለባቸው 16 የዓለማችን አገራት የመንግስታቱ ድርጅትን እንዲያግዛቸው ጠየቁ።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ጊዜ በአሜሪካ ተቅደም ፖሊሲያቸው በተቃራኒ የቆሙ አገራትን ለመቅጣት በመንግስታቱ ድርጅት በኩል ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
ይሁንና የቀድሞው ፕሬዘዳንት በድርጅቱ በኩል ፍላጎታቸው አልሰምር ሲላቸው በተናጠል በበርካታ አገራት ላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ቻይና፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ ቬንዙዌላ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች በርካታ አገራት በአሜሪካ የተናጠል ማዕቀቦች የተጣሉባቸው አገራት ናቸው።
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በትራምፕ የስልጣን ዘመን የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመሻር ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ማዕቀብ የተጣለባቸው አገራት ተስፋን ሰንቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ በአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ የተጣለባቸው 16 የዓለማችን አገራት የመንግስታቱ ድርጅትን እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።
እነዚህ ሀገራት ድርጅቱን የጠየቁት አዲሰየ የፕሬዘዳንት ባይደን አስተዳድር በቀድሞ ፕሬዘዳንት ትራምፕ የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመሻር ላይ በመሆኑ በእነሱም ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱላቸው ይፈልጋሉ።
እንደ አገራቱ ጥያቄ ከሆነ አገራት በተናጠል የሚጥሏቸው ማዕቀቦች የዓለምን ትብብር እና በጋራ የመስራት ባህሎችን ይጎዳል ይሄንንም ድርጊት የመንግስታቱ ድርጅት ሊያስቆም ይገባል የሚል ነው።
ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በትራምፕ የስልጣን ጊዜ ተወስነው የነበሩ በተለይም የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ወዳጅ አገራትን ያስቆጡ የተናጠል እርምጃዎችን በመቀልበስ ላይ ሲሆን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መመለስ፤ የዓለም ጤና ድርጅትን ዳግም መቀላቀል በባይደን የተቀለበሱ ውስኔዎች ናቸው።
አሜሪካ ከኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የባይደን አስተዳደር ስራ መጀመሩንም ዘገባው ጠቁሟል።