ጣሊያን 16 ሚሊዮን ዜጎቿን ከእንቅስቃሴ አገደች
ጣሊያን 16 ሚሊዮን ዜጎቿን ከእንቅስቃሴ አገደች
ኮሮና ቫይረስ ክፉኛ እየተፈታተናቸው ከሚገኙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ጣሊያን ቫይረሱ በተንሰራፋባቸው ሰሜናዊ ግዛቶቿ የሚገኙ 16 ሚሊዮን ያክል ዜጎች እንዳይንቀሳቀሱ አግዳለች፡፡
እገዳው ቫይረሱን ለመቆጣጠር በሚል የተወሰነ ሲሆን በስፍራዎቹ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ ከአካባቢው ለመውጣት ልዩ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ሎምባርዴን ጨምሮ ከ14 ግዛቶች መውጣትም ይሁን ወደ ግዛቶቹ መግባት አይቻልም፡፡
እርምጃው በዓለም ጤና ድርጅት ተደንቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም “የጣሊያን መንግስትና ህዝብ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስና ሀገራቸውን እንዲሁም ዓለምን ለመከላከል ጠንካራ እና አበረታች እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት ለሀገሪቱ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
ጣሊያን ወደ 6,000 ተጠቂዎች ሲኖሩባት ከ230 በላይ ሰዎች ሞተውባታል፡፡
በመላው ዓለም እስካሁን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3,500 በላይ ሲሆን ከ 105 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ከተጠቂዎች መካከል አብዛኛው ቁጥር የቻይና ሲሆን (80,859)፣ ደቡብ ኮሪያ ( 7,100)፣ ኢራን (6,566)፣ ዩ.ኤስ አሜሪካ (440) ይገኙበታል፡፡
በቻይና ዉሀን ግዛት ከሚገኙ 14 ጊዜያዊ የኮሮና ቫይረስ ህክምና ሆስፒታሎች ውስጥ 11ዱ መዘጋታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ በጊዜያዊ ሆስፒታሎቹ 12,000 ያክል ቀለል ያለ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ታክመዋል፡፡ ቀሪዎቸን 3 ሆስፒታሎችም በቀጣዮቹ 2 ቀናት ለመዝጋት ታስቧል፡፡
ከሁቤይ ግዛት ውጭ በቻይና ትናንት 3 የቫይረሱ ተጠቂዎች ብቻ የተገኙ ሲሆን ዛሬ ምንም ታማሚ አልተገኘም ነው የተባለው፡፡
ባጠቃላይ በቻይና እስካሁን 3,100 ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ 57,143 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡
በምስራቅ ቻይና ቁአንዡ ከተማ ደግሞ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች ተለይተው የተቀመጡበት ባለ 5 ፎቅ የሆቴል ህንጻ ተደርምሶ በጥቂቱ 10 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡
ከ70 በላይ ሰዎች ከነበሩበት ህንጻ ውስጥ እስካሁን ሟቾቹን ጨምሮ 48 ሰዎች ከፍርስራሹ የወጡ ሲሆን ቀሪዎቹን ለማግኘት ፍለጋው ቀጥሏል፤ የተለያዩ ምንጮች እንደዘገቡት፡፡