ትምህርት ቤቶች ግን እስከ ወርሃ መስከረም ተዘግተው ይቆያሉ ተብሏል
የጣልያን ፋብሪካዎች ከሳምንት በኋላ ስራ ይጀምራሉ
የኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ያደቀቃት ጣልያን ፋብሪካዎቿን እና ተዘግተው የቆዩ ህንጻዎቿን በቀጣዩ ሳምንት እንደምትከፍት ጠቅላይ ሚኒስትር ጉሴፔ ኮንቴ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉትን 2 ወራት የዘለቀው የእንቅስቃሴ ገደብ የሚነሳበትንና የተቀዛቀዘው ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴ የሚነቃቃበትን ፍኖተ ካርታ ትናንት ይፋ አድርገዋል፡፡
በፍኖተ ካርታው መሰረትም አምራቾች፣የግንባታ ተቋማትና ጅምላ ነጋዴዎች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ ይችላሉ፡፡ ቸርቻሪዎችም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ፡፡
ምግብና መጠጥ ቤቶች ደግሞ ወርሃ ሰኔ እስኪባጅ ድረስ መጠበቅ የግድ ይላቸዋል፡፡ እስከዛው ድረስ ግን የውጭ አገልግሎትን (takeaway) ለመስጠት ይቻላቸዋል፡፡
ጣልያን የቫይረሱን ስርጭት መግታትና አጠቃላይ የተጋላጭነት መጠኑን መቀነስ ባልቻለችበት ሁኔታ እገዳዎችን ለማንሳት ማሰቧ ለተጨማሪ ችግሮች እንዳይዳርጋት ግን ተሰግቷል፡፡
“ቀላል ፈተና እንደማይገጥመን እንጠብቃለን” ያሉት ኮንቴ “የምንኖረው ከቫይረሱ ጋር ሊሆን ይችላልና የትኛውንም አስፈላጊ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፓርኮች ሊከፈቱ እንደሚችሉ የሚያስቀምጠው ፍኖተ ካርታው ቤተሰቦች ቁጥራቸው ሳይበዛ እንዲጠያየቁ እና ከ15 ሰዎች በላይ የማይገኙበትን የቀብር ስነ ስርዓት ሊፈቅድ እንደሚችልም ያትታል፡፡
ሆኖም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሁንም ዝግ ናቸው፡፡ መንቀሳቀሱ የግድ ከሆነ ምክንያቱን በማሳወቅ ፍቃድ ማግኘትንም ይጠይቃል፡፡
ሙዚዬሞችና ቤተመጽሃፍቶች ከዛሬ 20 ቀን ጀምሮ ይከፈታሉ፡፡ ክለቦችም ልምምድ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ የሴሪዓ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊት ግን ሁኔታዎች በወጉ ሊጤኑ ይገባል እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፡፡
ትምህርት ቤቶችም እስከ አዲሱ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ እስከ ወርሃ መስከረም ተዘግተው ይቆያሉ፡፡
ወረርሽኙን ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ 3ኛውን ግዙፍ የአውሮፓ ምጣኔሃብት በእጅጉ ፈትኗል፡፡ ጣልያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ገጥሟት የማያውቀውን ዓይነት ችግርም ነው የተጋፈጠችው፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም ገደቦች ለቫይረሱ መፍትሄ እስኪገኝለት ድረስ እንደተጣሉ ይቆያሉ፡፡ሆኖም የቫይረሱ መፍትሄ ምናልባትም ጥቂት የማይባሉ ወራትን ሊወስድ ይችላል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ጣልያን እስካሁን ድረስ 27 ሺ ገደማ ዜጎቿን በቫይረሱ አጥታለች፡፡