ሩሲያ ለተጠባባቂ ጦሯ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ አሻቀበ
ሩሲያዊያን ያለ ቪዛ የሚበሩባቸው ሀገራት የጉዞ ትኬት ከዕጥፍ በላይ ጨምሯል ተብሏል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለ300 ሺህ ብሔራዊ ተጠባባቂ ጦር አባላት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል
ሩሲያ ለተጠባባቂ ጦሯ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ አሻቀበ።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በትናንትናው ዕለት ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር ከገባችበት ጦርነት ጋር በተያያዘ ለ300 ሺህ የብሔራዊ ተጠባባቂ ጦር አባላት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል ።
ይሄንን ተከትሎም ሩስያን ለቀው መውጣት የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ የጎግል ትሬንድን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ አቪያሴልስ የተሰኘው የሩሲያ የጉዞ ትኬት መግዣ ድረገጽ የአውሮፕላን ትኬት ፈላጊ በሆኑ ሩሲያዊያን መጨናነቁን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በተለይም ሩሲያዊያን ያለ ቪዛ መግባት የሚችሉባቸው ቱርክ እና አርመኒያ የአውሮፕላን ትኬት ለማግኘት ቢፈፋጉም ቲኬቶችን እስከ ቀጣዩ እሁድ ድረስ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ከሩሲያ በመውጣት ትራንዚት አድርገው ወደ ሌሎች ሀገራትም መብረር ያልተቻለ ሲሆን በተለይም ከዚህ በፊት እንደልብ የጉዞ ትኬት ይገኝባታል የምትባለው ጆርጂያም አሁን ላይ ትኬት ማግኘት እንዳልተቻለ ዘገባው ጠቅሷል።
በአጠቃላይ የፕሬዝዳንቱን ጥሪ ተከትሎ ከሞስኮ መውጣት የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር አሻቅቧል የተባለ ሲሆን ከሞስኮ ዱባይ ከዚህ በፊት ርካሽ የነበረው የጉዞ ትኬት አሁን ላይ ወደ 5 ሺህ ዶላር አሻቅቧል ተብሏል።
እንዲሁም ከዚህ በፊት የአንድ ጊዜ ጉዞ ትኬት ከሞስኮ አንካራ ቱርክ 22 ሺህ ሩብል የነበረው አሁን ወደ 70 ሺህ መጨመሩም ተገልጿል።
የሩሲያ ቱሪዝም ኤጀንሲ በበኩሉ በሩሲያዊያን ላይ ምንም አይነት የጉዞ እገዳ አለመጣሉን እና ዜጎች እንዲረጋጉ አሳስቧል።
የሩሲያ ብሔራዊ አየር መንገድ የሚባለው ኤሮፍሎት በበኩሉ ምንም አይነት የቲኬት ግዥ ክልከላም ሆነ የጉዞ እገዳ እንዳልተጣለ አስታውቋል።