ሩሲያ እና ጃፓን በሆካይዶ ደሴቶች የይገባኛል ጥያቄ የተነሳ የቆየ ቁርሾ አላቸው
የጃፓን 'ጸረ-ሩሲያ ትርክት' በሀገራቱ መካከል የሚደረጉ የሰላም ስምምነት ንግግሮችን ከባድ የሚያደርግ ነው ሲሉ የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሬ ሩደንኮ ተናገሩ፡፡
ሀገራቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ጀምሮ በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኙት የጃፓን ሰሜናዊ ጫፍ የሆካይዶ ደሴቶች ምክንያት የገቡበት እሰጥ አገባ እስካሁን በንግግር አልተፈታም።
ደሴቶቹ ሩስያ ኩሪልስ እያለች የምትጠራቸው ቢሆኑም ጃፓናውያን እንደ ሰሜናዊ ግዛቶች የሚቆጥሯቸው ናቸው፡፡
ሩደንኮ ለሩሲያው የዜና ወኪል /ታስ/ በሰጡት ቃለ ምልልስ " በግልጽ መልካም ያልሆኑ አቋሞች ከሚያራምድ እና በሀገራችን ላይ ቀጥተኛ ዛቻዎችን እንዲሰነዘሩ ከሚፈቅድ መንግስት ጋር የሰላም ንግግር ማድረግም ሆነ ስምምነት መፈራረም እንደማይቻል በጣም ግልጽ ነው” ብለዋል።
"በቶኪዮ በኩል ከጸረ-ሩሲያ አካሄድ ለመውጣት እና ሁኔታውን ለማስተካከል የሚደረጉ ሙከራዎችን እያየን አይደለም" ሲሉም አክለዋል ሩደንኮ፡፡
ሩሲያ ከጃፓን ጋር የነበራትን የሰላም ውይይት ያቋረጠችው ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ነበር፡፡
ውይይቱ የተቋረጠው ጃፓን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በያዘቸውን አቋም ምክንያት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ጃፓን የሞስኮን እርምጃ “ፍትሃዊ ያልሆነ” እና “ፍጹም ተቀባይነት የሌለው” ነው ስትል በወቅቱ ጠንካር ያለ ትችት መሰንዘሯና በዓለም አቀፉ ማህበረሰን ሲደረጉ ለነበሩ ማዕቀቦች ድጋፍ መስጠቷም ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በታይዋን ጉዳይ ላይ የቤጂንግን “አንድ ቻይና ፖሊሲ” እንደምትደግፍ ሩደንኮ ገልጸዋል፡፡
"ቻይናውያን በታይዋን ጉዳይ ላይ ሩሲያ ሁልጊዜ ከጎናቸው እንደሆነች ያውቃሉ" ነው ያሉት ሩደንኮ፡፡