ሰሜን ኮሪያ፣ የጃፓንን ወታደራዊ ግንባታ አደገኛ መዘዝ የሚያስከትል ነው ስትል አስጠነቀቀች
የፒዮንጊያንግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ከጃፓን ወታደራዊ ግንባታ እቅድ ጀርባ አሜሪካ አለችበት ብሏል
ፒዮንጊያንግ የጃፓን ወታደራዊ ግንባታን "አዲስ የማጥቃት ፖሊሲ" ብለዋለች
ሰሜን ኮሪያ ፤ የጃፓንን ወታደራዊ ግንባታ ተቸች፡፡
የፒዮንግያንግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፤ የቶኪዮ አዲሱ የደህንነት ስትራቴጂ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ፒዮንጊያንግ በተግባር ለማሳየት ዝግጁ መሆኗን የመንግስት ሚዲያ ዘግቧል ።
የሰሜን ኮሪያ ዛቻ የመጣው ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁን ወታደራዊ ግንባታዋን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ነው፡፡
የጃፓን ወታደራዊ ግንባታ እቅድ ትልቅ የተባለውን ቀጠናዊ ውጥረት የፈጠረ ነውም ተብሏል፡፡
የፒዮንጊያንግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደሚሉት ከሆነም የጃፓን አዲሱ ስትራቴጂ "አዲስ የማጥቃት ፖሊሲ"ና በምስራቅ እስያ የጸጥታ አካባቢ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አደገኛ እቅድ ነው፡፡
የጃፓንን ወታደራዊ ኃይል መልሶ በማቋቋም እና እንደገና የወረራ እቅድ በማውጣት ረገድ አሜሪካን ተጠያቂ ያደረጉት ቃል አቀባዩ፤ ዋሽንግተን ሰሜን ኮሪያ በራሷ ጥረት ወታዳራዊ አቅሟን ለማጠናከር በምታደርገው እንቅስቀሴ ጥያቄ የማንሳት ምንም መብት የላትም ብለዋል፡፡
“ጃፓን ምኞቷን ለማሳካት የምታደርገው ኢ-ፍትሃዊ እና ስግብግብ ሙከራ ምን ያህል እንደሚያሳስበንና እንዳበሰጨን ተግባራዊ ምላሽ ማሳየታችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ተናግረዋል ቃል አቀባዩ በይፋዊው የኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ በሰጡት መግለጫ።
በተያያዘ ተጽእኖ ፈጣሪዋ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ በሰጡት በሌላ መግለጫ ላይ ፒዮንግያንግ የስለላ ሳተላይት ለማምረት የምታደርገው ጥረት "ከደህንነታችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ “ በእኛ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል የዓለም አቀፍ ትብብር ትጮኻለች ” ያሉት ኪም ዮ ጆንግ፤ ነገር ግን በፒዮንጊያንግ ላይ ያነጣጠሩ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይህንን እቀድ ማቆም አይችሉም ብለዋል፡፡
“የመዳን እና የመልማት መብታችን አደጋ ላይ እየወደቀ ባለበት ሁኔታ ማዕቀብን ለምን እንፈራለን ... እና ለምን እናቆማለን? “ የሚል ጥያቄም አንስተዋል ተጽእኖ ፈጣሪዋ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ፡፡