ቻይና በታይዋን ላይ የደቀነችው ስጋት ጃፓን ወታደራዊ ወጪዋን እንድታሳድግ አስገድዷታል ተባለ
ጃፓን ከቻይናና ከሰሜን ኮሪያ ስጋት አንጻር ወታደራዊ ወጪዋን ማሳደግ እንዳለባት የጃፓን ባለስልጣን ተናረዋል
ታይዋንን የጎበኙበት የጃፓን ህግ አውጭው "አስጨናቂ እውነታ" መጋፈጥን አለብን ብለዋል
በታይዋን የሚገኙት የጃፓን ህግ አውጪ የቻይና ስጋት ሀገራቸው ተጨማሪ ወታደራዊ ወጪን እንድትመድብ ያስገድዳታል ብለዋል።
የጃፓን ገዥው ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከፍተኛ አባል ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ከደቀኑት ስጋትና "አስጨናቂ እውነታ" አንጻር ጃፓን ወታደራዊ ወጪዋን ማሳደግ አለባት ሲሉ ታይዋንን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ቻይና ይገባኛል የምትላት ታይዋን እና ጃፓን መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖራቸውም፤ ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት ግን አላቸው ተብሏል። ሁለቱም ስለ ቻይና በተለይም በሁለቱ ድንበር አቅራቢያ የሚደረግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያሳስባቸዋል።
የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የፖሊሲ ኃላፊ እና የቀድሞ የኢንዱስትሪ ሚንስትር ኮይቺ ሃጊዳ በታይፔ ጉብኝት ወቅት እንደተናገሩት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓን "በሰላም መንገድ እየተጓዘች ነው እና ይህ መንገድ ወደፊትም አይለወጥም።"
በጃፓን እና ታይዋን ግንኙነት ላይ በተካሄደው መድረክ "ነገር ግን ሰላም የሚለውን ቃል ብቻ ማንበቡ ሰላማችንን ለመጠበቅ ብቻውን በቂ አይደለም" ብለዋል።
ጃፓን የሚቀጥለውን ዓመት በጀት በምታዘጋጅበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የመከላከያ ወጪን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አንድ በመቶ የነበረውን በጀት በማንሳት በአምስት ዓመታት ውስጥ ሁለት በመቶ ለማድረግ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህም የጃፓን ዓመታዊ የመከላከያ በጀት ወደ 80 ነጥብ 55 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያደርሰዋል ተብሏል። ሀገሪቱ ይህ እርምጃዋ ከአሜሪካ እና ከቻይና ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ በጀት የምትመድብም ያደርጋታል።
ጃፓን የመከላከያ በጀቷን እንድታሳድግ ምክንያትነት የሆናት ቻይና በወታደራዊ ወጪዋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቷ እንዲሁም የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ መሆኑን ህግ አውጭው ጠቅሰዋል።
"ለእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ እውነታ ፊት ለፊት ምላሽ ለመስጠት ግማሽ እርምጃዎች ምንም ትርጉም የላቸውም" ብለዋል።
የጃፓን የመከላከል አቅም ህይወትን እና ሰላምን ለመጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሳይሆን በአፋጣኝ መጎልበት አለበት ሲሉም አክለዋል።
"ማንም አጥቂ ሊሆን የሚችል ሰው ሁለት ጊዜ እንዲያስብ ለማድረግ በቂ አቅም እንዳለን በግልፅ ማሳየት አስፈላጊ ነው" በማለት ወታደራዊ አቅምን ማፈርጠም የጃፓን የዛሬ የቤት ስራ መሆኑን አመላክተዋል።