ጃፓን በፈረንጆቹ 2030ዎቹ ሦስት ሽህ ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘጉ ሚሳይሎችን ልታለማ ነው
ጃፓን በዚህ ወር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁን ወታደራዊ ግንባታዋን ይፋ አድርጋለች
ለቶኪዮ በቀጣናው ያለው ውጥረት እና የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ስጋት ፈጥሮባታል ተብሏል
ጃፓን በፈረንጆቹ 2030ዎቹ ሦስት ሽህ ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘጉ ሚሳይሎችን ልታለማ ነው፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚንስቴር እስከ ሦስት ሽህ ኪሎ ሜትር የሚደርሱ በርካታ የረዥም ርቀት ሚሳይሎችን ለማምረት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
እ.አ.አ በ2030ዎቹም እነዚህን ሚሳይሎች የማሰማራት ዓላማ እንዳለ ኪዮዶ ዜና ለጉዳዩን ቅርብ ከሆኑ ምንጭ ሰማሁ ማለቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ቶኪዮ በፈረንጆቹ 2030ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሁለት ሽህ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሚሳይል እና ሦስት ሽህ ኪሎ ሜትር ሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ለማልማት ወጥናለች።
የዜና ወኪሉ እንደዘገበው ከሆነ በ2035 በሰሜን ኮሪያ እና አንዳንድ የቻይና አካባቢዎች አካባቢ ሊደርስ የሚችል ሚሳይል ለማሰማራት ፍላጎት አለ።
ጃፓን በቅርቡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁን ወታደራዊ ግንባታዋን ይፋ አድርጋለችም።
በ320 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ በጀት ለመበጀት እቅድ የያዘችው ጃፓን፤ ቻይናን መምታት የሚችሉ ሚሳይሎችን በመግዛት ለዘላቂ ግጭት ዝግጁ ለመሆን አቋም ይዛለችም ተብሏል።
ለሀገሪቱ ወታደራዊ አቅም መፈርጠም በቀጣናው ያለው ውጥረት እና የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ስጋት ስላለባት እንደሆነ ተነግሯል።