የጃፓን ፍርድቤት ለ48 አመታት የታሰሩት አዛውንት ከወንጀል ነጻ ናቸው ሲል ወሰነ
ኢዋኦ ሃካማዳ የተባሉት የ88 አመት አዛውንት በመርማሪዎች በተቀነባበረ ሀሰተኛ ማስረጃ ግማሽ ክፍለዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ታስረዋል
ሃካማዳ ያለጥፋታቸው የሞት ቅጣት ተላልፎባቸው እንደነበርም ተገልጿል
የጃፓን ፍርድቤት ለ48 አመታት የታሰሩት የቀድሞው ቦክሰኛ ኢዋኦ ሃካማዳ ለእስር የሚያበቃ ወንጀል አልፈጸሙም ሲል ወሰነ።
የ88 አመቱ ሃካማዳ በፈረንጆቹ 1966 ነበር በአራት ሰዎች ግድያ ጥፋተኛ ተብለው የታሰሩት።
የስራ ሃላፊያቸውን፣ ሚስትና ሁለት ልጆቻቸውን አቃጥለው ገድለዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ በ1968 ሞት እንዲቀጡ ተወስኖ እንደነበር የሚያወሳው የጃፓኑ ኤንኤችኬ፥ ክሱ በድጋሚ እንዲታይላቸው ያቀረቡት ተደጋጋሚ ይግባኝ የሞት ቅጣቱ ሳይፈጸም እንዲቀር ማድረጉን ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅት እድሜያቸው 91 አመት የደረሰው እህታቸው ሂደኮ ሃካማዳ ሳይሰለቹ ባደረጉት ጥረት በ2008 በድጋሚ ክሱ መታየት ጀምሮ በ2014 ከእስር ቤት መለቀቃቸውን ዘገባው አስታውሷል።
ሃካማዳ ከ48 አመታት እስር በኋላ የተፈቱት መርማሪዎች ያቀረቧቸው ማስረጃዎች በሀሰት የተቀነባበሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ መሆናቸው በመረጋገጡ ነበር።
ከጤናቸው ሁኔታ እና በእድሜያቸው ምክንያት ያመልጣሉ ተብሎ ስለማይታሰብ በቤታቸው ውስጥ ሆነው የእስር ጊዜያቸው ሲያሳልፉ የቆዩት ሃካማዳ በእህታቸው በኩል ሙሉ በሙሉ ከወንጀል ነጻ መሆናቸው እንዲወሰንና ነጻ እንዲወጡ ያደረጉት ጥረትም በዛሬው እለት ፍሬው ታይቷል።
የሺዙካ አካባቢ ፍርድቤት ባሳለፈው ውሳኔ የእድሜያቸውን ከግማሽ በላይ በእስር ቤት ያሳለፉት ኢዋኦ ሃካማዶ ወንጀለኛ አልነበሩም ብሏል።
ኮሺ ኩኒ የተባሉ ዳኛ ፍርድቤቱ ሃካማዶን ጥፋተኛ ለማድረግ በርካታ የሀሰት ማስረጃዎች ተቀነባብረው መግባታቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።
አዛውንቱ በአራት ሰዎች ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ ቢክዱም፥ በመርማሪ ፖሊሶች በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት ለማመን መገደዳቸውን ተናግረው ነበር።
ፖሊስ ሃካማዳ ግድያውን ሲፈጽሙ ለብሰውት የነበረና የደም ፍንጣቂ የነካካው ልብስ ግድያው ከተፈጸመ ከአንድ አመት በኋላ በሚሰሩበት ኩባንያ ውስጥ ተደብቆ ተገኝቷል ብሎ ማቅረቡንም የጃፓን ሚዲያዎች አውስተዋል።
ይሁን እንጂ የቶኪዮ ከፍተኛ ፍርድቤት በ2023 ከልብሱ ላይ የተገኙት የደም ናሙናዎች ከሃካማዳ የዘረመል ውጤት ጋር የሚመሳሰሉ አይደሉም በሚል የቀረበውን ማስረጃ ተቀብሎት ለጥፋታቸው የታሰሩትን ግለሰብ ከደሙ ንጹህ ናቸው ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ክሱን ያቀረቡት አካላት በሃካማዳ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔው እንዲተላለፍ ሲወተውቱ ቆይተዋል ነው የተባለው።
በዛሬው እለት ግን የ88 አመቱ ኢዋኦ ሃካማዳ ነጻነታቸው በይፋ ታውጆላቸዋል።
ለ48 አመታት የታሰረ ወንድማቸውን ለማስፈታት ብርቱ ትግል ያደረጉት ሂደኮ ሃኮማዳ “ኢዋኦ ብቻ አይደለም በርካታ ሰዎች በስህተት ታስረው እያለቀሱ እንደሚገኙ አምናለሁ፤ የወንጀለኛ ህጉ ይግባኝ መጠየቅን ቀላል በሚያደርግ መልኩ እንዲሻሻል እፈልጋለሁ” እፈልጋለሁ ብለዋል።
ከበለጹጉት ሰባት ሀገራት ውስጥ የሞት ቅጣትን እስካሁን ተፈጻሚ ማድረግ የቀጠሉት ሀገራት ጃፓን እና አሜሪካ ናቸው።
የጃፓን መንግስት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አብዛኛው ጃፓናዊ የሞት ቅጣትን እንደሚደግፍ ማመላከቱን ቪኦኤ ዘግቧል።