አሜሪካዊው ከ48 ዓመት እስር በኋላ በስህተት መታሰሩ ታወቀ
ሲታሰር የ22 ዓመት ወጣት የነበረው ይህ ሰው አሁን ላይ የ70 ዓመት አዛውንት ሆኗል
ግለሰቡ ለተፈጸመበት ስህተት 175 ሺህ ዶላር ካሳ እንደሚከፈለው ተገልጿል
አሜሪካዊው ከ48 ዓመት እስር በኋላ በስህተት መታሰሩ ታወቀ።
በአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ይኖር የነበረው ግሊን ፓሉምቦ የተሰኘው ግለሰብ ከ48 ዓመት በፊት ነበር በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ቁጥጥር ስር የዋለው።
ይህ ግለሰብ በወቅቱ የ22 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን ላለፉት 48 ዓመታት ከ18 ቀናት ጊዜውን በእስር ቤት አሳልፏል።
ፓሊምቦ የተጠረጠረበትን የግድያ ወንጀል እንዳልፈጸመ በተደጋጋሚ ለፖሊስ እና ፍርድ ቤቶች ቢናገርም ሰሚ አጥቶ ቆይቷል።
ይሁንና ከሰሞኑ ይህ ሰው የፈጸምከው ወንጀል የለም፣ ላለፉት 48 ዓመታትም የታሰርከው በስህተት ነው ተብሎ ከእስር ተለቋል።
ይህን ተከትሎም ጉዳዩ በመላው ዓለም ትኩረት የሳበ ጉዳይ የሆነ ሲሆን በታሪክ በስህተት ረጅም ዓመታት የታሰረ ሰው ለመባልም በቅቷል።
ግለሰቡ በስህተት በእስር ቤት ለቆየባቸው ዓመታትም 175 ሺህ ዶላር ካሳ እንደሚከፈለው ኒዮርክ ፖስት ዘግቧል።
አሁን ነጻ የተባለው ይህ አሜሪካዊ በአልኮል መጠጥ መሸጫ መደብር ውስጥ ሰው ገድሏል በሚል በከባድ ነውጥ እና ግድያ ወንጀል የሞት ፍርድ ተላልፎበት የነበረ ቢሆንም የአሜሪካ ህግ የሞት ፍርድን እንዳትፈጽም የሚገድብ ህግ መውጣቱን ተከትሎ ውሳኔው ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊቀየር ችሏል።