ለ10 አመታት በስህተት የታሰረው አሜሪካዊ 50 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ተወሰነ
የቺካጎ ፍርድቤት የ35 አመት እስራት ተፈርዶበት የነበረው ማርሴል ብራውን የደረሰበትን ጉዳት ሊያካክስ የሚችል ውሳኔ አሳልፏል
ፍርድቤቱ ፖሊስ ብራውን ያልፈጸመውን ግድያ እንዲያምን ማስፈራራቱንና ቤተሰቦቹን እንዳያገኝ ማድረጉን ገልጿል
በአሜሪካ ለአስር አመታት በሀሰተኛ ማስረጃ እንዲታሰር የተደረገው ወጣት የ50 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ተወሰነ።
ማርሴል ብራውን የተባለው የ34 አመት ወጣት በፈረንጆቹ 2008 ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
በፖሊስ ያስያዘው ጉዳይም በቺካጎ ምዕራባዊ ጫፍ የ19 አመት ወጣት ግድያ ነበር።
ብራውን የ35 አመት እስራት ተፈርዶበት አስር አመት በእስር ካሳለፈ በኋላ ግን በግድያ ወንጀሉ እጁ እንደሌለበት ተረጋግጦ በነጻ የተሰናበተው።
“ሎቪ ኤንድ ሎቪ” የህግ አማካሪ ተቋም ፖሊሶች በወቅቱ 18 አመቱን የያዘውን ብራውን በምርመራ ክፍል ውስጥ አስገብተው ከ30 ስአታት በላይ በጥያቄ ሲያስጨንቁት ነበር ብሏል።
ምንም አይነት ምግብና ውሃ ሳያቀርቡ፤ እንቅልፍ አሳጥተውና ስልክ ልደውል የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄውን ሳይቀበሉም ምርመራውን አድርገዋል ሲል ከሷል።
ፖሊስ ጥፋቱን አምኖ ቃሉን ካልሰጠ የእስር ቆይታው እንደሚረዝም ከማስፈራራት ባሻገር ሊረዱት የመጡትን ወላጅ እናቱን እና ጠበቃ እንዳያገኝ መደረጉን ተቋሙ አውስቷል።
ብራውን ከእስር ከተለቀቀ በኋላ “ህጻን ነበርኩ፤ በጣም በሚያስፈራ ስፍራ አስገብተው አስፈራሩኝ፤ ምንም ርህራሄ አላሳዩኝም” ሲል መናገሩን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ማርሴል ብራውን ለአስር አመት በእስር እንዲቆይ ምክንያት የሆነውና ገድሎታል የተባለው ወጣት በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ ማለፉ ሲረጋገጥ በ2018 ከእስር ተለቆ በ2019 ከወንጀል ነጻ መሆኑን የሚጠቁም የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።
ብራውን የመናገር ነጻነቴን ነጥቀው ያለጥፋቴ ለ10 አመት በእስር እንዳሳልፍ አድርገውኛል ያላቸውን የቺካጎ ከተማ ፖሊስ አዛዦች እና የኮክ ካውንቲ አቃቤ ህግን ከሷል።
ክሱን ሲመለከት የቆየው የቺካጎ ዲስትሪክት ፍርድቤትም ብራውን በፖሊሶች የተቀነባበረ ማስረጃ መታሰሩን ማረጋገጡን በመጥቀስ ለጉዳቱ 50 ሚሊየን ዶላር እንዲከፈለው ወስኗል።