በስህተት ለ43 አመት የታሰረችው አሜሪካዊት እንድትፈታ ተወሰነ
ሳንድራ ሄሚ በ20 አመቷ በግድያ ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባት ወንጀሉን የፈጸመውን ፖሊስ ለመሸሸግ ነው ተብሏል
ለ48 አመታት በስህተት የታሰረው አሜሪካዊ ባለፈው አመት መለቀቁ ይታወሳል
በአሜሪካ ለ43 አመታት በስህተት የታሰረችው ሳንድራ ሄሚ ከእስር እንድትለቀቅ ተወስኗል።
ሄሚ በፈረንጆቹ 1980 ፓርቲሺያ ጀስችኬ የተባለች እንስትን ገድላለች በሚል የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባት ነበር።
የሚዙሪ ፖሊስ የጀስችኬን ገዳይ ሲያፈላልግ ምርመራ ካደረገባቸው ሰዎች መካከልም በሀኪሟ ላይ ጥቃት ለማድረስ ቢላ ይዛ ያመራችው ሳንድራ ሄሚ አንዷ ነበረች።
ከ12 አመቷ ጀምሮ የአዕምሮ መታወክ ገጥሟት መድሃኒት የምትወስደው ሄሚ ለፖሊሶች ጀስችኬን “እኔ ነኝ የገደልኳት” የሚል ምላሽ ሰጥታ ነበር ይላሉ ጠበቃዋ።
ፖሊስም በቤቷ ውስጥ ጀርባዋ በስልክ ገመድ ታስሮ ሞታ የተገኘችው ጀስችኬ በወቅቱ የ20 አመት ወጣት የነበረችው ሄሚ እንደገደለቻት በመግለጽ ክስ ተመስርቶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባት ነበር ይላል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
በስህተት የታሰሩ ሰዎችን ለማስፈታት የሚንቀሳቀሰው “ኢኖሰንስ ፕሮጀክት” የተባለ ቡድን፥ ፖሊስ አስቀድሞ የደረሰው መረጃ እና ሄሚ “ገድያታለው” በሚል የሰጠችው ቃል የሚቃረን ቢሆንም የእስራት ውሳኔው ያለበቂ ማስረጃ በ1981 መተላለፉን ያወሳል።
ፖሊስ የሄሚን የአዕምሮ ጤና ችግር ያለአግባብ ተጠቅሞ ፍርድቤት በአንድ ቀን ውሳኔ አስተላልፏል ያለው “ኢኖሰንስ ፕሮጀክት”፥ ባለፈው አመት ለሊቪንግስተን ካውንቲ ፍርድቤት አቤቱታ አስገብቷል።
ባለፈው አርብም ዳኞች ሳንድራ ሄሚ ለ43 አመታት የታሰረችው ያለበቂ ማስረጃ ነው፤ በ30 ቀናትም ልትለቀቅ ይገባል የሚል ውሳኔን አሳልፈዋል።
በአሜሪካ ታሪክ በስህተት ለረጅም አመት በመታሰር ሄሚ ቀዳሚዋ ናት ያለው “ኢኖሰንስ ፕሮጀክት”፥ ከወንጀል ነጻ ሆና ለ43 አመታት በእስራት ያሳለፈችው ትክክለኛውን ገዳይ ለመደበቅ በተፈጸመ ሴራ መሆኑንም ይጠቅሳል።
ፓርቲሺያ ጀስችኬ በወቅቱ ፖሊስ በነበረውና በ2015 ህይወቱ ባለፈው ማይክል ሆልማን መገደሏን ማረጋገጥ መቻሉንም በመጥቀስ።
በአሜሪካ በስህተት ከሚፈጸሙ እስሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በመንግስት አመራሮች ያልተገባ ድርጊትና ወንጀልን ለመደበቅ ከሚደረግ ሙከራ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በ2020 የወጣ ጥናት ያሳያል።
በኦክላሆማ ባለፈው አመት ለ48 አመታት በስህተት የታሰሩት ጂልይን ሲሞንስ ወጣትነታቸውን በእስርቤት ጨርሰው መውጣታቸው ይታወሳል።
በሉይዚኒያም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ለ44 አመታት በእስር ቤት የቆየው ቪንሰንት ሲሞንስም በ2022 በስህተት መታሰሩ ታውቆ መፈታቱን ዋሽንግተን ፖስት አውስቷል።