ጃፓን የናሚቢያን "የዘንዶ ዋሻ" ማሰስ ጀመረች
ናሚቢያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያላት ሲሆን ከቶኪዮ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሀብቷን ለመጠቀም ያግዛታል ተብሏል
ጃፓን በ2021 ብቻ 173 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ማዕድናት ከውጭ ሀገር አስገብታለች
ጃፓን በደቡባዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ናሚቢያ የማዕድን ፍለጋ ጀመረች።
ሁለቱ ሀገራት በማዕድን አሰሳ እና ማውጣት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከአንድ ወር በፊት ተፈራርመዋል።
የናሚቢያው ሚነር ኢፓንጌሎ ኩባንያ ከጃፓን መንግስት የማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የማዕድን ፍለጋውን የሚያካሂደው "የዘንዶ ዋሻ" በተባለው ሰፊ ዋሻ ነው።
ሰፊ ሀይቅ አቅፎ የያዘው ይህ ዋሻ የማዕድን ክምችቱ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።
ጃፓን በዚህ ዋሻ የምታደርገው የማዕድን ልማት የብረትና ሌሎች ማዕድናት ፍላጎቷን እንደሚመልስ ነው የሚጠበቀው።
ቶኪዮ በዛምቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኮባልት እና ሌሎች ማዕድናትን ለማውጣት መስማማቷም ተገልጷል።
ጃፓን በታዳሽ ሃይል አበረታች ስራ እየሰሩ ከሚገኙ ሀገራት ተጠቃሽ ናት።
ሀገሪቱ ከፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ (ሶላር ፓኔል)፣ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ባትሪዎች በብዛት እያመረተች የከባቢ አየር ብክለት እንዲቀንስ አስተዋፅኦ እያደረገች መሆኑም ተገልጿል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ የሶላር ፓኔሎችን ለማምረት የሚውሉ ግብአቶችን ግን አብዛኛውን ከውጭ ነው የምታስገባው።
ሀገሪቱ በ2021 ብቻ 173 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ኒኬል፣ ሊቲየም እና ኮባልትናን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናትን ከውጭ ያስገባች ሲሆን፥ ይህም በማዕድን ግዥ ከአለም ሶስተኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓታል።
ጃፓን ማዕድናት የምታስገባው ከአውስትራሊያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር ነው።