የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ልዩ ትኩረት የሰጡት ውዱ ሃብት - ሊቲየም
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ተፈላጊነት እየጨመረ በመሄዱ ሀገራቱ የሊቲየም ባትሪ መስሪያ ፋብሪካዎችን እየገነቡ ነው
ቺሊ፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና እና ቦሊቪያ ከፍተኛ የሊቲየም ሃብት አላቸው
አሜሪካ እና ቻይና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመቆጣጠር ፉክክራቸው በቀጠለበት ወቅት የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ሃብታቸውን እሴት ጨምረው መሸጥ መርጠዋል።
በተለይም የሊቲየም እና መዳብ ሃብታቸውን በሚገባ ለመጠቀም አዳዲስ አሰራር እየተከተሉ ነው።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም የሊቲየም ሃብታቸውን ወደ ቻይና እና ሌሎች ሀገራት ይልኩ ነበር።
አሁን ግን በቻይና እና አሜሪካ የንግድ ውድድር ምክንያት ዋሽንግተን በምትጥለው ማዕቀብ ምክንያት ገበያቸው እየተጎዳ ነው።
በመሆኑም በዘርፉ የሚካሄደውን ልማት በመንግስት ብቻ የሚመራ እንዲሆንና ጥሬ እቃውን ከመሸጥ ይልቅ የሊቲየም ባትሪና ሌሎች ቁሳቁሶች በሀገር ቤት እንዲመረቱ እያደረጉ ይገኛሉ።
የአለማችን ቀዳሚዋ የመዳብ እና ሁለተኛዋ የሊቲኒየም አምራች ቺሊ ባለፈው ሚያዚያ ወር የሊቲየም ኢንዱስትሪዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ እንዲሆኑ መወሰኗ ይታወሳል።
ከቺሊ ቀደም ብላም ሜክሲኮ የሊቲየም ኢንደስትሪን በመንግስት ቁጥጥር ብቻ እንዲሆን ማድረጓ አይዘነጋም።
ዚምባቡዌ እና ኢንዶኔዥያም ለስልክ እና ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወሳኝ የሆነው ሊቲየም እሴት ሳይጨመርበት ከሀገራቸው እንዳይወጣ አግደዋል።
ሀገራቱ ጥሬ የሊቲየም ሃብታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን አምነው የተለያዩ ስራዎችን እየከወኑ ነው።
እንደ ኢንዶኔዥያ ያሉ ሀገራትም የሊቲየም ባትሪ ማምረቻ ፋብሪካ ገንብተው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ጀምረዋል።
በኢንዶኔዥያ የቻይናው ካቴል ኩባንያን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪን የሚያመርቱ ኩባንያዎች በቢሊየንን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
ከአለማችን የሊቲየም ሃብት ከ65 በመቶ በላዩን የያዙት በአርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ሜክሲኮ እና ቦሊቪያም የሀገራቱን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚይሳድጉ ማህብራት እየተቋቋሙ ነው።
የአለማችን ስምንተኛዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ብራዚል በቤጂንግ በበላይነት የተያዘውን ዘርፍ ለመፎካከር እየሰራች ነው ተብሏል።
በቺሊም በ290 ሚሊየን ዶላር የሊቲየም ባትሪ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑ ተገልጿል።
የደቡብ አሜሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሃብታቸውን በሚገባ እንዳይጠቀሙ ግን ግጭትና ጦርነቶች ሲያወኳቸው ይታያል።