ግሪንላንድ የአየር ንብረት ለውጥ ስሟን ያስቀይራት ይሆን?
80 በመቶ መሬቷ በበረዶ የተሸፈነው ግሪንላንድ በየአመቱ ከ250 ቢሊየን ቶን በላይ ግግር በረዶ እየቀለጠባት ነው
ጥናቶች ግሪንላንድ ከበርካታ አመታት በፊት እንደ ስሟ አረንጓዴ እንደነበረች አሳይተዋል
በጎግል ካርታ ግሪንላንድን ስንመለከት እንደ ስሟ “አረንጓዴ ምድር”ን አናይም።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ ያለ ግዙፍ ነጭ ደሴትን ነው የምንመለከተው።
ግሪንላንድ ስሟና ገጽታዋ ለየቅል ቢሆንም የቀደሙ ጥናቶች ግን እንዲህ በበረዶ ክምር ከመሞላቷ በፊት ልምላሜ የተላበሰች መሆኑን ያሳያሉ።
በሳይንስ ጆርናል ላይ የወጣ አዲስ ጥናት በግሪንላንድ ከ416 ሺህ አመት በፊት አረንጓዴ እጽዋት በስፋት እንደነበሩ አመላክቷል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ግሪንላንድ ልካ ነበር።
“ካምፕ ሴንቸሪ” የተሰኘ ጣቢያ ከፍታ የተለያዩ የምርምር ተግባራትን አከናውናለች። አሜሪካውያን በግሪንላንድ ጥልቅ ቁፋሮ በማድረግ የሰበሰቧቸውን በርካታ ናሙናዎች ወደ አገራቸው በመውሰድም ሲመራመሩባቸው ቆይተዋል።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከሀገሪቱ የተሰበሰቡ እንደ ዛፍ ቅጠል እና አልጌ ያሉ ናሙናዎች እስከ 2017 ድረስ ተጠብቀው መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ናሙናዎቹ በግሪንላንድ ከብዙ መቶ አመታት በፊት የሰው ልጆች ይኖሩ እንደነበር ማሳያ ተደርገው ቀርበዋል።
ኳርትዝ እና ፌድስታር የተሰኙ ማዕድናትም የተገኙ ሲሆን፥ በበረዶ መቅለጥ ምክንያት እየተሸፈኑ መሰወራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ከ424 ሺህ አመት በፊት የተከሰተ ከባድ ሙቀትም በረዶውን በማቅለጥ ግሪንላንድን በውሃ እንደሸፈናት ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት አለማችን እያስተናገደችው ያለው የአየር ንብረት ለውጥም የዴንማርክ ኪንግደም አካል የሆነችውን ሀገር በየአመቱ ከ250 ቢሊየን ቶን በላይ ግግር በረዶ እያቀለጠባት ነው ተብሏል።
ከሰማይ ነጭ ሆና የምትታየው ስሟ ግን “አረንጓዴ ምድር” የተሰኘችው ግሪንላንድ ከአለማችን ቀዝቃዛ ስፍራዎች ሁለተኛ ብትሆንም በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የአለም ሙቀት መጨመር ፈተና እየሆነባት ነው።