ቻይና ማዕድን ዘራፊዎችን ለሚጠቁሙ ሰዎች ሽልማት አዘጋጀች
ህገወጥ የማዕድናት ፍለጋ፣ ቁፋሮ እና ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ቤጂንግን ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱባት ነው ተብሏል
ቻይና ለየትኛውም ኢንዱስትሪ ወሳኝ የሆኑ ከ17 በላይ ማዕድናትን በማቅረብ ትታወቃለች
ቻይና ማዕድናትን በህገወጥ መንገድ የሚያወጡ አካላትን ለሚጠቁሙ ሰዎች ሽልማት ማዘጋጀቷ ተነገረ።
ቤጂንግ አስተማማኝ መረጃዎችን ለሚያቀርቡ ጠቋሚዎች ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ ነው ያስታወቀችው።
የሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽንም ህገወት የማዕድን ቁፋሮን ለመከላከል አዲስ ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን በቻይናው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ዊቻት ላይ አስፍሯል።
በዘመቻው በህገወጥ የማዕድን ፍለጋ፣ ቁፋሮ እና ሽያጭ የተሰማሩ አካላትን መጠቆምን የሚያበረታቱ ተግባራት ይከናወናሉ ተብሏል።
የብሉምበርግ መረጃ እንደሚያሳየው ቻይና ባለፉት 30 አመታት ከማዕድናት ንግድ ከፍተኛ ገቢ አግኝታለች።
ከሞባይል ስልኮች እስከ አውሮፕላኖች ድረስ ለየትኛውም ኢንዱስትሪ ወሳኝ የሆኑ ከ17 በላይ ማዕድናትን በማቅረብም ትታቀቃለች ብሏል ዘገባው።
ሀገሪቱ የእነዚህ ማዕድናት በብዛት መውጣትን ለመቀነስ እያንዳንዱ ማዕድን አውጪ በየአመቱ ሊያወጣ እና ሊሸጥ የሚችለውን ኮታ አውጥታ ለመገደብ ሞክራለች።
ምንም እንኳን ቁጥጥሩ ጠበቅ ያለ ቢሆንም ህገወጥ የማዕድናት ማውጣት እና ከሀገር የማስወጣቱ ሂደት እየጨመረ መሄዱ ቤጂንግን አሳስቧል።
ባለፈው ሳምንትም የቻይና የንግድ ሚኒስቴር እንደ ጋሊየም እና ገርማኒየም ያሉ ለሞባይል ስልክ ቺፕስ መስሪያነት የሚውሉ ማዕድናት ከነሃሴ ወር ጀምሮ ለውጭ ገበያ እንዳይውሉ ማገዱ ታውቋል።
ይህም እነዚህን ማዕድናት ከቻይና የሚያገኙ የምዕራባውያን የኤሌክትሮኒክስ አምራቾች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ብሉምበርግ አስነብቧል።