የጃፓን ፖሊስ አዛዥ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤ ግድያ ምክንያት ከስልጣን ሊለቁ ነው
የፖሊስ አዛዡ ኢታሩ ናካሙራ ፤ ከስልጣን የምለቀው “ለተፈጠረው ውድቀት ኃላፊነት ለመውሰድ ነው” ብለዋል
የአቤ ግዲያ ጥብቅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ያላት ጃፓን ያስተቸ አሳዛኘር ክስተት እንደነበር ይታወሳል
የቀድሞ የጃፓን ጠ/ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ግዲያ ማስቆም አልቻልኩም ያሉት የጃፓንፖሊስ አዛዥ “ከስልጣን መልቀቅ እፈልጋለሁ” አሉ፡፡
የጃፓን ፖሊስ አዛዥ አሰቃቂ በሆነው የቀድሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ግድያ እንዲከሰት ለተፈጠረው ክፍተት ኃላፊነት ለመውሰድ ከስልጣን እንደሚለቁ ማስታወቃቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የጃፓን ብሄራዊ ፖሊስ ኤጀንሲ ኃላፊው ኢታሩ ናካሙራ በሰጡት መግለጫ፤ ከስልጣን የምለቀው “ለተፈጠረው ውድቀት ኃላፊነት ለመውሰድ ነው” ብለዋል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት በሃምሌ ስምንት ላይ በቀድሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ለተፈጸመው ግዲያ በወቅቱ የነበረው የጸጥታ ጥበቃ የላላ ስለነበር መሆኑ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ይህም አሳዛኝ ክሰተቱን ተከትሎ የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ እና ሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ያመኑት ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የቀድሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ባሳለፍነው ሃምሌ 8፤2022 ለፓርቲያቸውበመቀስቀስ ላይ ሳሉ በሰሜን ምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍል ናራ ከተማ ጎዳና ላይ መገደላቸው ይታወሳል።
ግድያው ጥብቅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ያላት ጃፓን ልል የባለስልጣናት ጥበቃ ስርዓት እንዳላት ያጋለጠ ሲሆን የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም የፖሊስ መዋቅሯንም ያስተቸ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁት አቤ ጃፓንን ለሁለት ያህል ጊዜያት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ነበሩ።ስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲይዙ በእድሜ ትንሹ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።
አቤኖሚክስ በሚል ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናቸው ሃገራቸውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብትን ከገነቡ ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ ችለው የነበረም ሲሆን ጃፓን በተሻለ የዲፕሎማሲ እመርታ ላይ እንድትደርስ ስለማስቻላቸውም ይነገራል።
አቤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ በማድረግ የሃገራቸውን ጦር የማጠናከር ውጥናቸውን ሳይፈጽሙ ነው የተገደሉት።
ሆኖም ተተኪያቸው ኪሺዳ የሺንዞ አቤን ውጥኖች ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።