አቤ በጥይት ተመተው ሆስፒታል ገብተዋል
የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው።
ሺንዞ አቤ በምዕራባዊ ጃፓን በሚገኝና ናራ በተባለ ከተማ ጎዳና ላይ ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ከበስተጀርባቸው በተተኮሰ ሁለት ጥይት ደረታቸውን ተመተው ሆስፒታል ገብተዋል።
በተኩሱ አቤ ለህይወታቸው በሚያሰጋ የጤና ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን የዘገቡ የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች የ41 ዓመቱ የግድያ ሙከራው ፈጻሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
አቤ በተመቱበት ጊዜ ለሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳን በማድረግ ላይ ነበሩ።
'አቤኖሚክስ' በሚባል የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና የሚታወቁት ሺንዞ በጃፓን የመሪነት ታሪክ ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ቀዳሚው ሰው ናቸው።
አቤ ከሁለት ዓመታት በፊት ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትርነት መልቀቃቸው ይታወሳል።
በቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ የበርካታ ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው።