የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ይቅርታ ጠየቁ
በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ወቅት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለቀድሞ ረዳቶቻቸው ይቅርታ አድርገዋል ተብሏል
አቤ ይቅርታ የጠየቁት ከአሁን ቀደም አስተባብለውት በነበረው አንድ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው
የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከአሁን ቀደም አስተባብለውት በነበረው ጉዳይ ይቅርታ ጠየቁ፡፡
አቤ ከአሁን ቀደም ጽህፈት ቤታቸው ከሃገሪቱ ጥብቅ የፖለቲካ ህግ ውጭ የደጋፊዎቻቸውን ወጪ ሸፍኗል መባሉን አስተባብለው ነበር፡፡
ሆኖም ዛሬ በነበራቸው መግለጫ ጽህፈት ቤቱ ምን ሲሰራ እንደነበር በውል የማያውቁ ቢሆንም የሞራል ተጠያቂነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለሰጡት ማስተባበያ ሲመሩት የነበረውን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ይህንንም ነገ በሃገሪቱ ፓርላማ ቀርበው እንደሚያስረዱ ነው የገለጹት፡፡
ጃፓን ፖለቲከኞች ለደጋፊዎቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ የሚከለክል ጥብቅ ህግ አላት፡፡
አቤን እምብዛም የመጫን ፍላጎት እንደሌላቸው የተነገረላቸው የጃፓን ነገረ ፈጆች ሳይወራረድ በቀረ 40 ሚሊዬን የን (386 ሺ 210 ዶላር) ምክንያት በጸሃፊያቸው ሂሮዩኪ ሃይካዋ ላይ ክስ እያደራጁ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አቤ በገጠማቸው የጤና ዕክል ምክንያት ባሳለፍነው ወርሃ ነሃሴ መጨረሻ ስልጣናቸውን ለዮሺሂዲ ሱጋ ማስረከባቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተያያዘ ሌላ ዜና የስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ወቅት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቀድሞ ረዳቶቻቸው ይቅርታ አድርገዋል፡፡
ትራምፕ ይቅርታውን ያደረጉት ለቀድሞው የቀስቀሳ ዘመቻ አስተባባሪያቸው ፖል ማናፎርት እና ለቀድሞው አማካሪያቸው ሮጀር ስቶን ነው፡፡
ግለሰቦቹ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡበት ከ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ እና ሩሲያ በምርጫው ነበራት ከተባለው ጣልቃ ገብነት ጋር በተያያዘ ተከሰው ለእስር ጭምር ተዳርገውም ነበር፡፡
አማቻቸው እና ከፍተኛ አማካሪያቸው ለሆነው ለያሬድ ኩሽነር አባት ለሪል ስቴት ባለቤቱ ለቻርለስ ኩሽነርም በተመሳሳይ መልኩ ፕሬዝዳንትነታቸው የሚሰጣቸውን ስልጣን ተጠቅመው ይቅርታ አድርገዋል፡፡
ትራምፕ በድምሩ ለ26 ሰዎች ነው ትናንት ይቅርታ ያደረጉት፡፡ የ3 ተጨማሪ ሰዎች ቅጣትንም ከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወደሚሉ የቅጣት ደረጃዎች ቀይረዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ የቀድሞ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ፍላይንም ይቅር ከተባሉት መካከል ናቸው፡፡