የቀድሞው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከሁለት ቀናት በፊት ቅስቀሳ ላይ ሳሉ መገደላቸው ይታወሳል
ጃፓን ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሺንዞ አቤ ግድያ ሁለት ቀናት በኋላ ምርጫ ማካሄድ ጀመረች።
ምርጫው የተወካዮች የላይኛው ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ የሚካሄድ ነው።
ጃፓናውያን ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ድምጽ መስጠት ጀምረዋል ።
የሀገሪቱ መሪ ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የማሸነፉን ቅድመ ግምት አግኝቷል።
የቀድሞ ሊቀመንበሩን ግድያ ተከትሎ የተሻለ ድጋፍን ሊያገኝ እንደሚችልም ነው የተገመተው።
የቀድሞው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከሁለት ቀናት በፊት ለፓርቲያቸው በመቀስቀስ ላይ ሳሉ በሰሜን ምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍል ናራ ከተማ ጎዳና ላይ መገደላቸው ይታወሳል።
ግድያው ጥብቅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ያላት ጃፓን ልል የባለስልጣናት ጥበቃ ስርዓት እንዳላት ያጋለጠ ሲሆን የፀጥታና ደህንነት እንዲሁም የፖሊስ መዋቅሯንም ያስተቸ ነው።
ከአሁን በኋላ በሚደረጉና ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዎ ኪሺዳን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት በሚገኙባቸው ቅስቀሳዎች የቪ.አይ.ፒ ጥበቃዎችን ማጠናከር እንደሚገባትም ነው የተነገረው።
በሺንዞ አቤ ግድያ የሚቆም ዲሞክራሲ እንደሌለ የተናገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዎ ኪሺዳም በአቤ መኖሪያ ቤት ተገተኝተው ቤተሰቦቻቸውን አጽናንተዋል።
በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁት አቤ ጃፓንን ለሁለት ያህል ጊዜያት በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
ስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲይዙ በዕድሜ ትንሹ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።
አቤኖሚክስ በሚል ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናቸው ሃገራቸውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብትን ከገነቡ ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ ችለው የነበረም ሲሆን ጃፓን በተሻለ የዲፕሎማሲ እመርታ ላይ እንድትደርስ ስለማስቻላቸውም ይነገራል።
አቤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ በማድረግ የሃገራቸውን ጦር የማጠናከር ውጥናቸውን ሳይፈጽሙ ነው የተገደሉት።
ሆኖም ተተኪያቸው ኪሺዳ የሺንዞ አቤን ውጥኖች ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።