ቶም ቱጌንዳት ቦሪስ ጆንሰንን ተክተው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችል ተገለጸ
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንደሚለቁ መግለጻቸው ይታወሳል
ቦሪስ ጆንሰን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል
ቶም ቱጌንዳት ቦሪስ ጆንሰን ተተኪ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችል ተገለጸ።
የ49 ዓመቱ የወግ አጥባቂ ፓርቲ የህግ አውጪ ምክር ቤት አባል የሆኑት ቶም በትናንትናው ዕለት ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ያስታወቁትን የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ተክተው እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የቀድሞው የብሪታኒያ ወታደር ቶም ቱጌንዳት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል።
ቶም ሀገራቸውን በወታደርነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በተለይም የሀገራቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ በኢራቅ እና አፍጋኒስታን የዘመቱ ሲሆን አሁን ላይ በብሪታኒያ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ምክር ቤት የመከላከያ ዘርፍን በረዳትነት እያገለገሉ ሲሆን፤ ከዚህ ያለፈ የመንግስት ተቋማትን በመምራት ልምድ የላቸውም የሚሉ ትችቶች እየተነሱባቸው ይገኛል።
የእንግሊዝን ከአውሮፓ ህብረት መውጣት በመቃወም የሚታወቁት እኝህ ፖለቲከኛ በፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል።
ቴሌግራፍ ለተሰኘው የሐገሪቱ ጋዜጣ ስለቀጣይ እቅዳቸው ዙሪያ በሰጡት ቃለመጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
“ህዝባችን ግልጸኝነትን ያረጋገጠ መንግስታዊ አስተዳድር እና አገልግሎትን ይፈልጋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ከተመረጥኩ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል ስራዎችን እሰራለሁ፣ በመንግስት እና ዜጎች መካከል መተማመንንም እፈጥራለሁ” ሲሉም እጩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በግብር ከፋዮች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አድርገዋል ያሉት ቶም ለዚህ ምላሽ እንደሚሰጡ፣ ከብሬእግዚት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ መዛነፎችን እንደሚያስተካክሉም አክለዋል።
የፈረንሳዊ ዜግነት ካላት ባለቤታቸው የተወለዱ የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ቶም ፈረንሳዊ እና እንግሊዛዊ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሲሆን እንግሊዛውያን እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የሆኑት ሱዌላ ብራቨርማን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት እንደሚወዳደሩ ያሳወቁ ሲሆን የሀገሪቱ ወግ አጥባቂ ፓርቲ በሚቀጥለው ሳምንት ቀጣዩን መሪ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።