አሜሪካ ለፕሬዝዳንት ፑቲን የ‘እንነጋገር’ ጥሪ ምላሽ ሳትሰጥ ቀረች
ባይደን ‘ፑቲን ገዳይ ነው’ በሚል የሩሲያ አቻቸውን በንግግር መወረፋቸው የሚታወስ ነው
“አሜሪካ የፕሬዝዳንት ፑቲንን ጥሪ አለመደገፏ የሚያስቆጭ ነው”- ሩሲያ
አሜሪካ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቀረበውን የ‘እንነጋገር’ ጥሪ ሳትደግፍ ቀረች፡፡
ሞስኮው በዚህ የዋሽንግተን ምላሽ ቅር መሰኘቷን አስታውቃለች፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ጋር በሁለትዮሽና ሌሎች የግንኙነት ጉዳዮች ላይ የበይነ መረብ ንግግር ለማድረግ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
ንግግሩ ምናልባትም እ.ኤ.አ መጋቢት 19 ወይም ዛሬ መጋቢት 22 ሊካሄድ እንደሚችልም ነበር ፑቲን ያስታወቁት፡፡
ሆኖም ባይደንም ሆነ መንግስታቸው ለጥሪው ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል እንደ ሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፡፡
ዋሽንግተንም ጥሪውን በተመለከተ እስካሁን በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡
ይህ “የሚያስቆጭ” እንደሆነ በመግለጫው የጠቆመው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች መካከል የሚያጋጥሙ ችግሮችን “ለማረቅ” ያስችል የነበረው “እድል” አምልጧል ሲል አስታውቋል፡፡
ለዚህ ሙሉ ኃላፊነቱ የአሜሪካ እንደሆነም ነው በመግለጫው የጠቆመው፡፡
ሩሲያ ‘ፑቲን ገዳይ ነው፤ ለዚህም የእጁን ያገኛል’ ለሚለው ሰሞንኛ የፕሬዝዳንት ባይደን ንግግር ግንኙነታችንን የሚያጠለሽ በጣም መጥፎ ንግግር ነው በሚል ጠጠር ያለ ምላሽ መስጠቷ የሚታወስ ነው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር በሚል የአሜሪካ አምባሳደሯን ጠርታ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ባይደን ከኤቢሲ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛው ጆርጅ ስቴፋኖፑሎስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው ስለ ፑቲን ገዳይነት የተናገሩት፡፡
ባይደን በዚህ ንግግራቸው ይጸጸቱ እንደሆነ የተጠየቁት የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ምንም ዐይነት የሚጸጽት ንግግር እንዳልተናገሩና በጋዜጠኛው ለተጠየቁት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡
የፑቲን የ‘እንነጋገር’ ጥሪም ይህን የባይደንን ንግግር ተከትሎ የቀረበ እንደነበርም ይታወሳል፡፡